ቀጥታ፡

አዲስ ስፖርት ፓርክ የጀግኖች መዘከሪያ እና የትውልድ መገንቢያ ስጦታ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ ስፖርት ፓርክ የጀግኖቻችን ክብር ህያው የሚሆንበት፣ የነገዋን ኢትዮጵያ በጤናማ ትውልድ የምንገነባበት ታላቅ ስጦታ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተውና በዓለም መድረክ ለሀገራቸው የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ ጀግኖች አትሌቶች መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባው አዲስ ስፖርት ፓርክ ዛሬ ተመርቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ጥሪ የተደረገላቸው ጀግኖች አትሌቶች በተገኙበት ፓርኩ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት በከተማዋ እምብርት በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል፣ ሁሉንም ዓይነት የስፖርት ዘርፎች ያካተተ ነው ብለዋል።

ፓርኩ የነገዋን ኢትዮጵያ በአካልና በሞራል የታነጸ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለጀግኖች አትሌቶች የክብር መግለጫ፣ ለወጣቶች የተስፋ ምንጭ፣ ለልጆች ደግሞ የደስታ ስጦታ ሆኖ መቅረቡን አመልክተዋል።

የፓርኩ ልዩ ገጽታ በኦሎምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የኢትዮጵያን ስም ላስጠሩ 15 የምንግዜም እንቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የቆመው የክብር ሐውልት እንደሆነም አንስተዋል።

ይህም ጀግኖችን በቁም ለማመስገንና ለተተኪው ታዳጊ ትውልድ እኔም እችላለሁ የሚል ትልቅ የስነ-ልቦና ተነሳሽነት ለመፍጠር ታስቦ የተከናወነ መሆኑን ነው ከንቲባዋ የገለጹት።

ፓርኩ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚመጥን መልኩ የተገነባ ሲሆን፣ ለባለሙያዎችና ለወጣቶች የኦሎምፒክ ደረጃቸውን የጠበቁ የመዋኛ ገንዳዎች፣ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችን መያዙን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ስፖርትን የዘወትር የሕይወት ዘይቤ ለማድረግ የሚያግዙ ዘመናዊ የቤት ውስጥና የውጪ ጂም፣ የዌልነስ ሴንተር (Wellness Center) እና የ800 ሜትር የመሮጫ ትራክ ተካትተውበታል።

ለልጆችና ለታዳጊዎች ደግሞ እንደ እድሜያቸው የተዘጋጁ ዘመናዊና ባህላዊ የመጫወቻ ስፍራዎች፣ የመዋኛ ገንዳዎችና የአሸዋ ላይ ስፖርት ሜዳዎች ተገንብተዋል።

መሠረተ ልማቶቹ ህጻናት በአካልና በአዕምሮ እንዲያድጉ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል።

ይህ የልማት ፕሮጀክት ከስፖርት ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ያጠናክራል ያሉት ከንቲባዋ በተለይም ለካዛንችስ አካባቢ የልማት ተነሺዎች የተገነቡ የሴራሚክ መሸጫ ሱቆች፣ የዜጎችን ኑሮና ስራ ከልማቱ ጋር ለማስተሳሰር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

በተጨማሪም 300 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ ሁለት ቤዝመንት የመኪና ማቆሚያ፣ የአውቶቡስ ተርሚናል፣ እስከ 3 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ ሰፊ ፕላዛ እና ምቹ ሬስቶራንቶች ፓርኩን ለቤተሰብና ለጎብኚዎች ተመራጭ እንደሚያደርጉት ነው ያብራሩት።

ፓርኩ ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር ተሰናስሎ የተሰራ በመሆኑ፣ የአረንጓዴ ልማት መናፈሻውና የውሃ ፋውንቴኑ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ አረንጓዴ ከተማ ለማድረግ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ ስፖርት ፓርክ የፅናትና የብልጽግና ምልክት መሆኑን ገልጸው ከተማዋን ውብና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም