ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው የከተማዋን የኮሪደር ልማትና የከተማ እድሳት ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን ዛሬ በይፋ መርቀው ከፍተዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው የከተማዋን የኮሪደር ልማትና የከተማ እድሳት ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን ዛሬ በይፋ መርቀው መክፈታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።

‎በ5.7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሁሉን አቀፍ ፕሮጀክት፤ የኦሎምፒክ ደረጃን ያሟላ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ እና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችን እንዲሁም የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን፣ ዘመናዊ የቤት እና የዉጪ ጂም ጨምሮ በርካታ ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ከማህበረሰብ አገልግሎቶች ጋር አቀናጅቶ የያዘ ነው።


 

ልማቱ ሁሉንም የእድሜ ክልሎች ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ የልጆች መጫወቻዎችን፣ እንደ እድሜያቸው የተከፋፈሉ መዋኛ ገንዳዎች፣ የአሸዋ ላይ የእጅ እና የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎችን እና የጤና ማዕከልን አካቷል።

በኦሎምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶች በፓርኩ መሐል መቆማቸው፤ የጀግኖቻችንን ታሪክ ሕያው ከማድረግ ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ ስፖርተኞች ታላቅ ተምሳሌት ይሆናሉ።


 

ከስፖርታዊ አገልግሎቶች ባሻገር፣ ፕሮጀክቱ 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ፕላዛ ከሬስቶራንቶች እና ካፌዎች ጋር፣ 300 መኪናዎችን በአንዴ የሚይዝ ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት መኪና ማቆሚያ እና በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የተገነቡ 105 የንግድ ሱቆችን አካትቷል።

ከወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ጋር የተሳሰረው ይህ ፓርክ፣ ነዋሪዎችን በመዝናኛም ሆነ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊና ሁለገብ የከተማ ፕላን ማሳያ ነው።

ይህ ያለመችውን የምታሳካዋ፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ገጽታ ነው!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም