ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የአፈር ለምነትን መጠበቅ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቷል

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ለምነትን መጠበቅ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው "የአፈር ለምነትንና ጤናማነትን ማስጠበቅ ለግብርና ሽግግር" በሚል መሪ ሃሳብ 14ኛው ዙር ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተካሂዷል።

በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አክበር ጩፎ(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው የአፈር ለምነትን መጠበቅ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

የአፈር ለምነትና ጤናማነትን መጠበቅ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድግ በመሆኑ ለግብርና ዘርፍ ምርምሮች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎችን በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡


 

ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ ከ79 ሚሊየን ብር በላይ በጀት በመመደብ ከ50 በላይ የምርምር፣ 54 የማህበረሰብ ተኮር እንዲሁም ከ14 በላይ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዘውድነህ ቶማስ(ዶ/ር) ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው ያለውን ዕውቀት ከሀብት ጋር ለማቀናጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በዚህም የዘንድሮው 14ኛው ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ የአፈር ጤንነትና ምርታማነት ላይ አተኩሮ መዘጋጀቱን ጠቁመው በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራንና ባለሙያዎች ቅንጅታቸውን በማጠናከር የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል አበክረው መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የአፈር ሳይንስ ጥናት ፕሮፌሰር ፋኑኤል ላዕከማርያም ፅሁፍ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በአፈር ዙሪያ የሚደረጉ ምርምሮች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር የሰው፣ የአካባቢ እና የእንስሳትን ጤና ለማስጠበቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።

በጥናታዊ ጽሁፋቸው የአፈር እርጥበትን ማስጠበቅ፣ አሲዳማነትን መቀነስ፣ ምርታማነትን መጨመርና ካርቦንን አምቆ የመያዝ አቅምን ማሳደግ ላይ ያተኮረ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም የተለያዩ ጥናቶች መስራታቸውን ጠቁመው ይህም መንግስት ዘርፉን ለማሻሻል የጀመረውን ውጥን የሚደግፍ በመሆኑ ወደ አርሶ አደሮች በማምጣት እንደሚተገበርም አስረድተዋል።


 

በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና የአየር ንብረጥ ለውጥ መቋቋም ፕሮግራም ዳይሬክተር አወቀ ሙሉዓለም(ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው የሀገሪቱን ግብርና ለማሻገር በጥናት የተደገፈ ስራ በመስራት የግብርናን ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ መንግስት በዘርፉ የያዘውን ውጥን ለማሳካት እየተጋ መሆኑን በመጥቀስ ለስራው ውጤታማነት ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይህም አርሶ አደሩ ከቤተሰብ ፍጆታ ያለፈ ትርፍ ምርት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም ገበያን በማረጋጋት በኩል አበርክቶ እንዲኖረው ትልቅ ድርሻ መወጣቱን አመልክተዋል።

በመድረኩ ከ10 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ሙያዊ ውይይት ተደርጎ የፖሊሲ አቅጣጫ የማመላከት ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም