በክልሉ የገበያ ማእከላት ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የገበያ ማእከላት ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እያቀረቡ ነው
ባህርዳር፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተገነቡ የገበያ ማዕከላት ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዋጋን በማረጋጋት አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በባህርዳር ከተማ የገበያ ማዕከል የግብርና ምርቶች በስፋት የቀረቡበት የትንሳኤ ዋዜማ ባዛር ዛሬ ተከፍቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አትክልት አሳቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የተገነቡ ማዕከላት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኝት ገበያ ለማረጋጋት እያስቻሉ ነው።
በክልሉ በ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በጀት በስምንት ሪጂዮፖሊታን ከተሞች የተገነቡት የገበያ ማዕከላት የግብርና ምርትን በብዛት፣ በአይነትና በጥራት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
የገበያ ማዕከላቱ አምራቹ እና ሸማቹ በቀጥታ ተገናኝተው የሚገበያዩበት በመሆኑ በህገ-ወጥ ደላሎች ይፈጠር የነበረውን የዋጋ ንረት በማስቀረት ለህብረተሰብ እፎይታን የሰጠ ነው ብለዋል።
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፤ የገበያ መእከላቱ ዋጋን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው ባዛርም አምራችና አቅራቢዎች ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሸጡ ከማስቻሉም በላይ ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል የግብርና ምርቶች መዳረሻ ገበያ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተዋቸው ወርቁ፤ ባዛሩ የተከፈተበት የባህርዳር ከተማ የገበያ ማዕከል ስራ በጀመረ በ2 ሳምንት ውስጥ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት አከናውኗል ብለዋል።
ዛሬ በተከፈተው ባዛርም 120 አምራቾችና አከፋፋዮች ምርቶቻቸውን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረባቸውን ነው የገለጹት።
የባዛሩ አላማም ጥራት ያለውና ደህንነቱ የተረጋገጠ የምግብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ህብረተሰቡ የትንሳኤ በዓልን አቅሙ በሚፈቅደው መሰረት እንዲገበያይ የሚያደርግ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በባዛሩ ላይ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ ዱቄት፣ እንቁላል፣ ጤፍና ሌሎች የምግብ ምርቶች መቅረባቸውን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
እስከ ትንሳኤ በዓል ዋዜማ በሚቆየው ባዛርም በግብርና ምርቶች መዳረሻ ገበያ ማዕከል፤ በባህርዳር ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ የተዘጋጀ መሆኑ ተመልክቷል።