ቀጥታ፡

አዲስ ስፖርት ፓርክ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በፈጣን የግንባታ አፈጻጸም ተገንብቶ የተጠናቀቀውና ለከተማዋ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው አዲስ ስፖርት ፓርክ ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ መንግሥት ለዜጎች ጤና እና ለከተማዋ ዘመናዊ ገጽታ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት እንደሆነም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት እና የአረንጓዴ መዝናኛ ስፍራ፣ ከግንባታ ፕሮጀክትነት ባለፈ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እውነተኛ ገጽታ መገለጫ መሆኑን አመልክቷል።


 

ማዕከሉ የከተማዋን ነዋሪዎችና ጎብኝዎችን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን አሟልቶ የተገነባ እንደሆነ ተገልጿል።

በፓርኩ ውስጥ ከተካተቱት ዋና ዋና መሰረተ ልማቶች መካከል የኦሎምፒክ ደረጃን የሚያሟላ የመዋኛ ገንዳ፣ የ800 ሜትር የሩጫ ትራክ፣ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎች ይገኙበታል።

ከነዚህም በተጨማሪ ለሕፃናት መጫወቻ የሚሆኑ ስፍራዎችና ልዩ የአሸዋ ሜዳዎች ለማህበረሰቡ ዕረፍት እንዲውሉ ተዘጋጅተዋል።

የቀጣዩን ትውልድ ለማነቃቃትና የሀገር ባለውለታዎችን ለመዘከር፣ በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ የ15 አንጋፋ አትሌቶች የክብር ሐውልቶች በፓርኩ ውስጥ መቆማቸው ልዩ ትርጉም ሰጥቶታል።


 

ይህም ስፍራው የስፖርት ማዘውተሪያ ብቻ ሳይሆን የታሪክና የጀግንነት መዘከሪያ እንዲሆን ያደርገዋል።

ማዕከሉ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለፈ ለንግዱ ማህበረሰብ ሰፊ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆች ተካተውበታል።

በተጨማሪም በአንድ ጊዜ 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ መገንባቱ፣ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኩነቶች ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም