ቀጥታ፡

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ተራዘመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሲያከናውን የቆየውን የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ማራዘሙን አስታወቀ።

ቦርዱ ቀደም ሲል ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን መታቀዱን አስታውሷል።

የምዝገባ ሂደቱን በቴክኖሎጂ ለማገዝ በወጣው ዕቅድ መሠረትም የዕጩዎች ምዝገባ በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁንና የመራጮች ምዝገባ ደግሞ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሲከናወን መቆየቱን ገልጿል።

ሆኖም በምዝገባ ሂደቱ ወቅት በተወሰኑ አካባቢዎች በቴክኖሎጂ የታገዘውን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ የኔትወርክ አቅርቦት ችግር ማጋጠሙን ቦርዱ ገልጿል።

ይህንን ተግዳሮት በመቅረፍ ሂደቱን አስተማማኝና ቀልጣፋ ለማድረግ የተጠቀመውን ተጨማሪ ጊዜ ለማካካስ የምዝገባውን ጊዜ ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል።

በተጨማሪም አስተማማኝ የኔትወርክ አቅርቦት ይኖራቸዋል ተብለው በታሰቡ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የኔትወርክ መቋረጥ በማጋጠሙ፣ ሂደቱን ወደ ማኑዋል (በእጅ) አሠራር በመቀየር ረገድ የባከነውን ጊዜ ለመተካት መወሰኑን በመግለጫው አመልክቷል።

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በነበረ የትራንስፖርት ችግር ምክንያት የምዝገባ ቁሳቁሶች በወቅቱ ባለመድረሳቸው ለተፈጠረው መዘግየት ምላሽ ለመስጠት፣ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባው ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም ማድረጉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም