ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በያዝነው ዓመት መድኃኒት የማምረት አቅሟን ከ50 በመቶ በላይ ታደርሳለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ መድኃኒት የማምረት አቅሟን፣ በ2018 ዓ.ም ከ50 እስከ 55 በመቶ ለማድረስ ማቀዷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከልን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ ሀገር ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል መቀየር እጅጉን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት፣ አፍሪካ ለከፍተኛ አደጋ ትጋለጣለች የሚል ግምት በበለጸጉት ሀገራት በኩል የነበረ ቢሆንም፣ ያ ሳይሆን መቅረቱን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ዝግጁነት ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ማለፉን ተናግረዋል።


 

በወቅቱ መንግስት በምግብ፣ በልብስ እና በመድኃኒት ዘርፎች ራስን መቻል አለብን የሚል ግልጽ አቅጣጫ ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በዚህም በምግቡ ዘርፍ ስንዴን ጨምሮ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ በመድኃኒት በኩል ግን በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አለመታየቱን ጠቁመዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማምረት የምትችለው መድኃኒት ስምንት በመቶ ብቻ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በቂ የመድኃኒት ምርት ማምረት አለመቻሉ፣ ሻጮች የግዢ መድኃኒት መያዛቸውና የግሉ ዘርፍ በምርት ሂደቱ ላይ ለመሳተፍ እምብዛም ፍላጎት አለማሳየቱ በመንግስት በኩል ትልቅ ቁጭት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

በምግብ፣ በልብስና በመድኃኒት ራሱን ያልቻለ ሀገር የተሟላ ሉዓላዊነት እንደሌለው ጠቅሰው፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን አመልክተዋል።


 

ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ማምረት የምትችለው የመድኃኒት ድርሻ ቀደም ሲል ከነበረበት ስምንት በመቶ አሁን ላይ ወደ 44 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜያት የሚመረቁ ፋብሪካዎችን ታሳቢ በማድረግም በተያዘው ዓመት የማምረት አቅሙ ከ50 እስከ 55 በመቶ እንደሚደርስም አስታውቀዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ቢያንስ መድኃኒትና ክትባትን በራሷ አቅም እንድታመርት  በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአንጋፋው የአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም የተመረቀው ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ከፍተኛ ወጪ የወጣበት መሆኑን ጠቁመው፣ ለማዕከሉ ለመድኃኒትና ክትባት ምርት መሠረት የሚጥሉ ዕውቀቶችን መያዙንም አመልክተዋል።

በኮቪድ ወቅት የናሙና ምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይላክ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አዲሱ የምርምር ማዕከል እንዲህ ያሉ ምርመራዎችን እዚሁ የማከናወን አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ማዕከሉ 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስና ባዮኢንፎርማቲክስ ክፍሎችን እንዲሁም የመድኃኒቶችን ጥራት የሚያረጋግጥ የባዮኢኩዊቫለንስ ማዕከልን ያካተተ ሲሆን፤ ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች ምላሽ የመስጠት አቅምን በመገንባት ረገድም እንደ ዋልታ የሚያገለግል መሆኑን አመልክተዋል።

ምርምርን ወደ ፖሊሲ፣ ፈጠራን ደግሞ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር ረገድ ማዕከሉ በመድኃኒት ምርት ራስን ለመቻልና ዘላቂ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በጥረትና በትጋት ከሰራን ሀገርን ማሳደግና ማበልጸግ እንደሚቻል ይህ ማዕከል ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም