ለልማት የሚለቀቅ የመሬት ይዞታ ላይ የሚታዩ የካሳ ክፍያና ቅሬታ አቀራረብ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለልማት የሚለቀቅ የመሬት ይዞታ ላይ የሚታዩ የካሳ ክፍያና ቅሬታ አቀራረብ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር ይገባል
አዳማ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ለልማት የሚለቀቅ የመሬት ይዞታ ላይ የሚታዩ የካሳ ክፍያና ቅሬታ አቀራረብ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባ የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መሬት በሚለቀቅበት ወቅት በካሳ፣ በመልሶ ማቋቋምና በቅሬታ አቀራረብ ላይ በማተኮር የዘርፉ ምሁራን በተሳተፉበት የምርምር ሲምፖዚየም በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በመድረኩ እንደገለጹት፤ መንግሥት የሀገሪቱን የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት በገጠርና በከተማ ለማዘመን በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር በወረቀት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለሙስና፣ ለሀብት ምዝበራና ለተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች የተጋለጠ እንደነበር አስታውሰዋል።
የመሬት ይዞታ ለልማት በሚለቀቅበት ወቅት የሚታዩ የካሳ ክፍያና የቅሬታ አቀራረብ ችግሮችን ለመፍታት፣ የፍትሕና ባለድርሻ አካላት የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ዜጎች ለይዞታቸው ሕጋዊ ዋስትና እንዲያገኙ የዲጂታል ይዞታ ማረጋገጫ (ካዳስተር) ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን፣ ፍትሐዊ የካሳ አከፋፈል እንዲኖር የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን በበጎ የሚታይ መሆኑን አንስተዋል።
ዘመናዊ አሰራሩ የይገባኛል ጥያቄዎችንና ግጭቶችን ከመቀነሱ ባለፈ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታየውን የክርክር መጨናነቅ ማቃለሉን ገልጸዋል።
ሕጎችንና አሰራሮችን ማዘመን ብቻውን በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የሕጎቹን ተፈጻሚነትና ውጤታማነት በምርምር በመደገፍ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማቅረብ ይገባል ብለዋል።
የሪፎርሙን ውጤታማነት ለመገምገም የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።