የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምላሽ የሚሻ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምላሽ የሚሻ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምላሽ የሚሻ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ነው ሲሉ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) አመለከቱ።
የኦሮሚያ ክልል የሕግ ማሠልጠኛና ምርምር ኢንስቲትዩት 4ኛው ሀገር አቀፍ የጥናት ሲምፖዚየም ላይ "ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ያላት መብት" በሚል ርዕስ በቀረበ የመወያያ ጽሑፍ ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ እየገነባቻቸው ባሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች መጠን በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ፣ ሀገሪቱ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የነበራትንና በፖለቲካ ሴራ ያጣችውን የባህር በር፣ ልክ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ሁሉ በተባበረ ኃይል ጥረት በማድረግ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምላሽ የሚሻ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የሚቀጥል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ጥያቄውን በሕጋዊና በሳይንሳዊ መንገድ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት በሁሉም አካላት ሊደገፍ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል የሕግ ማሠልጠኛና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አዱኛ አህመድ፤ ኢንስቲትዩቱ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር የተለያዩ ጥናቶችንና የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘንድሮም የሀገሪቱን ወቅታዊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ በባህር በር መብት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት በማቅረብ ሲምፖዚየሙ መከፈቱን ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያ በሕጋዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የምታከናውነውን እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር ያግዛል ብለዋል።
የባህር በር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር አለበት ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው።
የኢንስቲትዩቱም ይህንን ሀገራዊ ጉዳይ በጥናትና ምርምር ለመደገፍ የጀመረው ጥረት ለሌሎች ተቋማትም ምሳሌ የሚሆን መሆኑን ተናግረዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አምባሳደር ሌንጮ ባቲ፤ የባህር በር ከሀገር ሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ብሔራዊ ጥቅም እና መብትን ለማስከበር የባህር በር ያስፈልጋል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተው በቀረበው መነሻ ጽሁፍ ላይ ውይይት አድርገዋል።