መጋቢት 24 የሶማሌ ክልል ህዝብ ትክክለኛ ውክልና ያገኘበትና አዲስ የፖለቲካ ባህል የታየበት ዕለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጋቢት 24 የሶማሌ ክልል ህዝብ ትክክለኛ ውክልና ያገኘበትና አዲስ የፖለቲካ ባህል የታየበት ዕለት ነው
ጅግጅጋ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ መጋቢት 24 የሶማሌ ክልል ህዝብ ትክክለኛ ውክልና ያገኘበትና አዲስ የፖለቲካ ባህል የታየበት ዕለት ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገለጸ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ መጋቢት 24 የሶማሌ ክልል ህዝብ ትክክለኛ ውክልና ያገኘበትና አዲስ የፖለቲካ ልምምድ የጀመረበት ዕለት ነው ብለዋል።
ከለውጡ የሶማሌ ክልል የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ችግሮች የነበሩበት መሆኑን አስታውሰው ከለውጡ ወዲህ ለችግሮቹ መፍትሄ በመገኘቱ በክልሉ አሁን ላይ ውጤታማ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ሪፎርሞች በክልሉ ሁለንተናዊ ልማት እየተረጋገጠ መሆኑን ገልፀው ከአግላይና ከፋፋይ የፖለቲካ ሥርዓት በመውጣት አዲስ የፖለቲካ ባህል መታየቱንም አክለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ አንስተው በክልሉ በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በጠቅላላ ምርጫው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚወዳደሩም ገልጸዋል።
በጸጥታና በፍትህ ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውንና የማጠናከር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን በመጥቀስ በቀጣይም በክልሉ የሚገኙ ፀጋዎችን በተገቢው መንገድ መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በክልሉ ተግባራዊ የተደረጉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ዘርፈ ብዙ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው ህብረተሰቡን በሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
ክልሉን የቱሪዝም የስበት ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች በውጤታማነት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ማህበረሰቡን ከተረጂነት ለማውጣት የተጀመሩ የግብርና ልማት ሥራዎች የበለጠ እንደሚጠናከሩም አረጋግጠዋል።