ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፉ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል

ደብረ ማርቆስ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፡- በለውጡ ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፉ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ተመስገን ተድላ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ የተካሔደው ለውጥ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱ አበረታች እድገት እንዲመዘገብ አድርጓል።

በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንቨስትመንት ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ በማድረግ የተሻለ የሚባል ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል ነው ያሉት።

ለአብነትም በ2010 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩይንቀሳቀሱ የነበሩት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 200 ብቻ እንደነበሩ አመልክተው በአሁኑ ወቅትም ቁጥራቸው ከአንድ ሺህ 100 በላይ መድረሱን ገልፀዋል።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ተኪ ምርት በማምረትና ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማስፋት አንፃር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

በካፒታል ደረጃም በዘርፉ የነበረው ዝቅተኛ የሀብት ፍሰት እንደነበር አመልክተው በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ ተግባራትም የሀብት ፍሰቱን ከ34 ነጥብ አራት ቢሊየን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹም የአምራች ኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የቱሪዝም፣ የአገልግሎትና ሌሎች ዘርፎች እንደሚገኙበት አስገንዝበዋል።

ወደ ስራ የገቡት ፕሮጀክቶችም ከ16 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሰራ እድል ለመፍጠር መቻላቸውንም  አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ከ120 ሄክታር በላይ መሬት ከሶስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በጋፖ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ደርብ ወርቁ እንደገለጹት፤በከተማው የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለበርካታ ወጣቶች መልካም እድል ይዞ መጥቷል።

በፋብሪካው ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እንዳስቻላቸው ጠቁመው የኢንዱስሪዎች መስፋፋት አማራጭ የስራ  እድልና የተሻለ ክፍያ በሚያገኙበት መስክ ለመስራት እንዳስቻለቸው ተናግረዋል።

 ከባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ  በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ የተመረቀውና በሰላም ዱቄት ፋብሪካ ሰራ የተፈጠረለት ወጣት ድረስ ውዴ በበኩሉ ፤የፋብሪካዎቹ መስፋፋት በፍጥነት ወደ ስራ ለመሰማራት እንዳስቻለው ነው የሚገልፀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም