ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከካርበን ግብይት መስፈርቶች ጋር የሚጣጣሙ የደን አያያዝ ስራዎችን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የካርበን ግብይት መስፈርቶች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬትና የደን አስተዳደር ልምዶችን እያሳደገች መሆኑን የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የካርበን ክምችት መኖሩን በማንሳት፤ አብላጫው በደን ሀብት ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ሀገሪቱ ከካርበን ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር የጎላ ሚና እየተጫዎተ እንዳለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የብዝሃ ህይወት ባለቤት በመሆኗ የተሻለ የካርበን ክምችት ለመያዝ የሚያስችል ተስማሚ ሥነ-ምህዳር እንዳላት ዶክተር አደፍርስ ገልጸዋል። 

ሀገሪቱ በአየር ንብረትና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ካርበንን ከአየር ላይ በማስወገድ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ መንገድ እንዲከማች እያደረገ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በደን መመንጠርና ባልተገባ የመሬት አያያዝ ምክንያት ወደ ህዋ ይለቀቅ የነበረውን ሙቀት አማቂ ጋዝ መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካይነት እየተተገበሩ እንዳለ አስረድተዋል።

በዚህም ከካርበን ግብይት መስፈርቶች ጋር የሚጣጣሙ ዘላቂ የመሬት እና የደን አሥተዳደር ልምዶችን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል። 

ሁለተኛው ደግሞ እጽዋት በሚተከሉበት ወቅት ቀደም ሲል ወደ ህዋ የሄደውን ካርበን አምቀው የሚመልሱበትን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ እና ከልቀት የተጠበቀውን ካርበን ገበያ ለማቅረብ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት የካርበን ሽያጭን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንና ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የግዢ ውል ስምምነት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የኖርዌይ መንግስት እንደመነሻ የ75 ሚሊዮን ዶላር የካርበን ግዢ እንዲሁም የዓለም ባንክም እንዲሁ የግዢ ውል ማሰሩን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ኖርዌይ እና የዓለም ባንክ ሊገዙት ከሚፈልጉት በላይ ካርበን ማመንጨቷን ጠቁመው፤ እስከ አንድ ቢሊየን ዶላር ሊያመጣ የሚችል ካርበን ሀብት መኖሩን ገልጸዋል። 

በዓለም ገበያ ላይ ለካርበን ግዢ የሚመደበውን ከፍተኛ ሀብት ወደ ኢትዮጵያ የካርበን ሽያጭ ማምጣት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። 

በዓለም ላይ ያለውን የካርበን ፋይናንስ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከማጠናከር ባለፈ ሰነዶች የማደራጀትና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

 

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም