ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን

አዳማ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።   

ፌዴሬሽኑ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ሥልጠና መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።   


 

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ትዕግሥት ተረፈ እንደገለጹት፤ ሴቶች በምርጫ ሂደት ያላቸው ተሳትፎ ከጎለበተ ፍትሐዊ፣ ነፃና አሳታፊ የምርጫ ምኅዳር ለመፍጠር መሠረታዊ ነው።   

"ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በመጠቀም የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቷ፤ ከቤተሰብ ማስተዳደር ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ተሳትፎ ድረስ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።   

ፌዴሬሽኑ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጮች ግንዛቤ ለመፍጠርና በታዛቢነት ለመሳተፍ ፈቃድ ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።   

እስካሁንም እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ለበርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ በመላ ሀገሪቱ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።   

የዛሬው መድረክም ከኦሮሚያ ክልልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አመራሮችና አባላትን ያሳተፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።   

የምርጫ ታዛቢዎች የሕዝብ አመኔታን ለመጨመር፣ የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማሻሻልና የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

የሴቶች ማኅበራት የታዛቢነት ሚናቸውን መወጣታቸው ምርጫው ተዓማኒ እንዲሆንና የዴሞክራሲ ባህል እንዲጠናከር እንደሚረዳም አክለዋል።   


 

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ፌዴሬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እጸገነት ሙሉጌታ በሰጡት አስተያየት፤ ሴቶች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሚናቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።   

ሌላዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ መስከረም አንበሴ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው በምርጫ ሥነ-ምግባርና በታዛቢነት መርሆዎች ላይ ያጠነጠነ በመሆኑ የተጣለባቸውን ሕዝባዊ አደራ በኃላፊነት ለመወጣት አቅም እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።   


 

በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች በምርጫው ዕለት በየምርጫ ጣቢያው በመገኘት ለመብታቸው የሚቆሙ ዕጩዎችን እንዲመርጡና ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም