በጠቅላላ ምርጫው የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለንን ካርድ ወስደናል- የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው የሚበጀንን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለንን ካርድ ወስደናል- የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች
አርባምንጭ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፡- በጠቅላላ ምርጫው የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለንን ካርድ ወስደናል ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ ለመራጮች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ነዋሪዎች በቀሪው ጊዜ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ መውሰድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ/ም የሚካሄድ ሲሆን ለዚሁም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የምንፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችል ካርድ ወስደናል ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተረፈ አልበኔ እንዳሉት በምርጫው ለመሳተፍ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ በመሆኑ የሚበጀኝን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ነው ያሉት።
የጊዜ ሰሌዳው እየተጠናቀቀ በመሆኑ ካርድ ያልወሰዱ በቀሩት ጥቂት ቀናት ካርድ መውሰድ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ወ/ሮ አሰለፈች አሽኔ በበኩላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል።
አቶ ማሩ ሞታ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መተግበሪያ በመጠቀም በኦን ላይን መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የመራጮች የምዝገባ ሂደት እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከናወን መሆኑን ቦርዱ ካወጣው መርሃ ግብር መረዳት እንደሚቻል ገልፀው ካርድ ያልወሰዱ ነዋሪዎች በቀሪው ጊዜ ሊወስዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።