ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው

ደሴ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየተደረገ ባለው ጥረት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) አስታወቁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እና በስታርታፕ ፖሊሲ አዋጅ ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሁለንተናዊ እድገትን ለማፋጠን በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት ለዚህ አጋዥ የሆኑ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እቅድን በስኬት ለማጠናቀቅ ማስቻሉን አውስተዋል።

በተለይም በሪፎርም ማሻሻያዎችና በተቋማት ግንባታ፣ በመሠረተ ልማትና በሰው ኃይል ልማት፣ በኢንተርኔት ተደራሽነትና በዲጂታል ክፍያ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎች ቁልፍ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማበረታታትና ወደ ተግባር እንዲገቡ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ መሪ እንድትሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህ ውጤታማነትም ሚኒስቴሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ የዛሬው መድረክም የተጀመሩ ተግባራትን ማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አወል ሰይድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ አሠራር በቴክኖሎጂ ከመደገፍ ባለፈ፣ የሌሎች ተቋማትን አቅም በመገንባት የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ እንዲሳካ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ካሳ ሻውል(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሀገር እድገት መሠረት በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎታል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት አገልግሎቱን ማዘመን መቻሉንና ሂደቱን በጥናትና ምርምር እያገዙ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በመድረኩ ከወሎ፣ ከመቅደላ አምባ፣ ከወልድያ፣ ከራያ እና ከሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም