ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከልን መርቀው ከፈቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከልን መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከልን ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአርማወር ሐንሰን የምርምር ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባው ይህ ዘመናዊ ተቋም ከመሠረተ ልማት ግንባታ ባለፈ፤ ራሷን የቻለችና ጤናማ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚተጋ የላቀ የዕውቀት ማዕከል ነው ብለዋል።
የምርምር ማዕከሉ 40 ላቦራቶሪዎችን፣ የላቁ የጂኖሚክስ (genomics) እና የባዮኢንፎርማቲክስ (bioinformatics) ቦታዎችን፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራትና ብቃት የሚያረጋግጥ የባዮኢኩዊቫለንስ (bioequivalence) ማዕከልን ማካተቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ ለድንገተኛ አደጋዎች ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት አቅምን በመገንባት ረገድ እንደ ማገር ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ምርምርን ወደ ፖሊሲ፣ ፈጠራን ደግሞ ወደ ተግባራዊ መፍትሔ በመቀየር፤ ይህ ማዕከል በመድኃኒት ምርት ራሳችንን ለመቻል፣ ዘላቂ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉም ገልጸዋል።