በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ማበረታቻዎችና ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ማበረታቻዎችና ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ) ፡-በሐረሪ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ማበረታቻዎችና ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በሐረር ከተማ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት በማድረግ በሐረር ከተማ በመገኘት የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተመልክቷል።
በሐረር ቆይታው ዓለም አቀፍ የጀጎል ቅርስንና በከተማው የተገነቡ ኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎችን ከርእሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ ጋር በመሆን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን በሚሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ዙሪያም ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ውይይት አድርጓል።
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ በውይይቱ ወቅት በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ማበረታቻዎችና ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አንስተዋል።
በተለይ አልሚ ባለሃብቶችን የማበረታታት፣ የመደገፍና የማገዝ ተግባራት የማጎልበት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመሆኑም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በሐረር ከተማ ለሚያደርገው ኢንቨስትመንት ተመሳሳይ እገዛ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ሐረር ከተማ የእድሜ ባለጸጋና የቱሪስት ከተማ መሆኗን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን፤ በከተማዋ ዘመናዊ የእንግዶች ማረፊያዎችን መገንባትና ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የሚገነባው የሆቴልና ሪዞርት ኢንቨስትመንት ለከተማዋ ትልቅ እምርታ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ፤ ጥንታዊና ታሪካዊ የመስህብ ስፍራ ባለቤት የሆነችው ሐረር ከተማ በተለይም ለሆቴልና ሪዞርት ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ተናግሯል።
ከዚህ ባለፈም በከተማው በተገነቡ ውብና ማራኪ የኮሪደር ልማት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የልማት አማራጮች ለዘርፉ ልማት ትልቅ እድል ስለመሆናቸው አንስቷል።