ቀጥታ፡

ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሀገራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥና ምርጫውን ለማሳካት የሚያስችል አቅም ገንብቷል

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሀገራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥና ምርጫውን ለማሳካት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም መገንባቱን የክልል  ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የፀጥታና መረጃ ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የክልል ርዕሳነ- መስተዳደሮች የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሀገራዊ ደኅንነትን ለማረጋገጥና ሰባተኛውን ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ጉብኝት ማድረጋቸውን አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች በሰጡት አስተያየት፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ በቦታና በጊዜ ሳይገደብ መረጃዎችን የመሰብሰብና የመተንተን ብቃቱ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በየትኛውም ስፍራ የሚከሰቱ ማናቸውም የፀጥታና ደኅንነት ስጋቶችን በመለየት ተንትኖ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥበት የማድረግ አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትኩረት በመስጠት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና ድኅረ- ምርጫ ወቅት የደኅንነት ስጋቶች ቢያጋጥሙ ቀድሞ ለመለየትና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን በጉብኝታቸው ወቅት ማረጋገጣቸውን አብራርተዋል፡፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም የተለያዩ ተዋንያን ሚናም ወሳኝነት ስላለው ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

"የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ቅንጅት ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት" በሚል መሪ ሀሳብ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባዘጋጀው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፈረንስ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል።


 

በመድረኩም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችና የፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም