ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረግን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረግን ነው
ጅማ ፤መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደም በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረጉ መሆኑን የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎች ተናገሩ።
የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፎች ስኬቶችን በተግባር ያረጋገጠበት ስኬታማ አመት መሆኑን በብዙ ማሳየዎች መግለጽ ይቻላል።
የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ሰላማዊ ትግል እያደረጉ እና የመንግስት ተቋማትን የመምራት እድል የተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም በማስቀደም በሃሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች ገልጸዋል።
የሸካ ዞን የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሀይሉ ተስፋዬ፤ ከለውጡ በፊት በፖለቲካው ለመሳተፍ ባደረጉት ጥረት በጠላትነት ተፈርጀውና ተገፍተው መቆየታቸውን አስታውሰው በለውጡ በተፈጠረው ምቹ ምህዳር በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖርም በሀገር ብሄራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር ላይ የጋራ አቋም ያላቸው መሆኑን አንስተው ከማይገባ ተቃርኖ እና የጠላትነት እሳቤ በመውጣት በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በተፈጠረው ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ፉክክር እያደረግን ለዘንድሮውም ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስተባባሪ አቶ ሰለሞን መኮንን፤ ለውጡ በተለይም የፖለቲካውን ምህዳር በማስፋት እና አሳታፊ በማድረግ የሚታይና ተጨባጭ ውጤት የመጣበት ሆኗል ብለዋል።
በፖለቲካ ፉክክሩ በሀገር ብሄራዊ ጥቅም ላይ የጋራ አቋም መኖሩን አንስተው ከገዢው ፓርቲ ጋር ስለ ሀገር እና የዜጎች ጉዳይ ላይ ተቀራርበን እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እያደገ እንዲመጣ ኢዜማ የበኩሉን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።