የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተገበረ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማስፈን የደንበኞችን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አሰራሮችን እየተገበረ እንደሚገኝ ገለጸ።
መንግሥት የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህም እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያሉ በአጭር ጊዜ የህዝብን የእርካታ መጠን ማረጋገጥ የቻሉ ተቋማትን መገንባት ተችሏል።
ይህን መሰረት በማድረግ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም አሰራራቸውን በማዘመንና ከህዝብ ጋር በመቀራረብ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የሚያስችል ስልት እየተከተሉ ይገኛል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ዳይሬክተር ህብረወርቅ ይመኑ፣ ተቋሙ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ደንበኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚገጥሟቸውን ብልሹ አሰራሮችን በምስጢር መጠቆም የሚችሉበትን ቀላል፣ ምቹ እና ደህንነቱ የተጠበቀ መተግበሪያ ስራ ላይ ማዋሉን አስታውቀዋል።
በዚህም ደንበኞች "eeuethics.et" በተሰኘው ድረ-ገጽ በመግባት ወይም መተግበሪያውን ስልካቸው ላይ በመጫን ቅሬታቸውንና ጥቆማቸውን በቀላሉ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
መተግበሪያው የደንበኞችን የጥቆማ ተሳትፎ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ 374 ጥቆማዎች መቅረባቸውን አብራርተዋል።
ከጥቆማዎች መካከል በማጣራትም በተገኙ ግኝቶች መሠረት በ98 ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ተቋሙ ለጠቋሚዎች ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ብልሹ አሰራሮችን በድፍረት እንዲያጋልጡ የሚያስችል የእውቅና አሰጣጥና የጥበቃ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱንም ገልጸዋል።
የአሰራር ስርዓትን በቴክኖሎጂ ከማዘመን ባለፈም የሰራተኞችን የስነ-ምግባር ሁኔታ ለመለየት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ደንበኞች ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ለማንኛውም አገልግሎት ክፍያ ሲፈጽሙ ህጋዊ ደረሰኝ የመቀበል ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።