ቀጥታ፡

ለግብርና ትራንስፎርሜሽንና ሜካናይዜሽን የተሰጠው ትኩረት ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ መሰረት እየጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለግብርና ትራንስፎርሜሽንና ሜካናይዜሽን የሰጠችው ትኩረት ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ መሰረት እየጣለ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

የ2018/19 የሰብል ልማት ንቅናቄ "በምርትና ምርታማነት የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መፃኢ ጊዜ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ ብሩህ ነው።

በመደመር መንግሥት የተጀመረው የግብርና ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በተጨባጭ ውጤት መታየት መጀመሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ግብርና ዘመናዊ በማድረግ ወደ ሜካናይዜሽን እየተሸጋገረ መምጣቱን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ተግባር ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

የ2018/19 የመኸርና የበጋ ሰብል ልማት  ወቅት በዓለም አቀፍ ቀውስ ፈተና ውስጥ ሆና የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ በማስገባት ስጋቱን መሻገር መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይም የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የሎጂስቲክ ስርዓቱን ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቋቋም  ሌት ተቀን በትጋት መሥራት ይገባናል ብለዋል።


 

የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ፈተናዎችን ወደ ዕድል የቀየርንበትን ልምድ ዛሬም ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከ33 በላይ ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።

ክልሎች ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ በመተግበር በትጋት መስራት ከተቻለ ለውጥ እንደሚመጣ ኢንሼቲቮች በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ያሉ ልምዶችን በመውሰድ ዝርያዎችን በማላመድ ዓይነት ብዙ ምርቶችን ማምረት መጀመሩን ገልጸው፤ ከአማራ ክልል ልምድ በመቅሰም ሩዝ ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም