ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ጅማ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ነመራ ቡሊ ገለጹ።

በጅማ ዞን ኦሞ ናዳ ወረዳ አሰንዳቦ ከተማ፣ በወረዳ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
 
አቶ ነመራ ቡሊ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ በስፋት እየተተገበረ መሆኑንና የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሂደት ለመመለስ እየተከናወነ ያለ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።



 
አገልግሎቱ ብልሹ አሰራሮችን ከማስቀረት ባለፈ፣ የህዝቡን ጥያቄዎች አንድ በአንድ እየመለስን ለመሆናችን ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ወደፊትም አገልግሎቱን በማዘመን ለበርካታ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
 
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፣ የዞኑ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን ለመፍታት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በወረዳ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል። 
  
የአሰንዳቦ ከተማ አስተዳዳሪ ነዚፍ ሼህ ከማል በማዕከሉ 11 ተቋማት 52 ዓይነት አገልግሎቶች በ8 መስኮቶች እንደሚሰጥ ጠቅሰው ባለሙያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም