የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይጠቅመናል ብለን የምናምንበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይጠቅመናል ብለን የምናምንበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች
ጅግጅጋ፣መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይጠቅመናል ብለን የምናምንበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ቀን ተወስኖ፣ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ስም እንዲሁም የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል ለመወሰን የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት አካሒዷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹም ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የምርጫ ክርክርና የቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የኢዜአ ሪፖርተር በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተዘዋውሮ የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ያሉ ዜጎችን አነጋግሯል።
ከየምርጫ ጣቢያዎቹ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎችም የምርጫ ካርድ በመውሰድ በምርጫው እለት በድምፃቸው የሚመራቸውን ፓርቲ ለመወሰን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ አብዱላሂ ሀሰን እና አቶ ሙክታር ከድር፤ የምርጫ ሂደት የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት መሆኑን በማንሳት በእለቱ ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የምርጫ ካርድ ከመያዝ በተጓዳኝ ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት ሁላችንም የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናልም ብለዋል።
ሌላኛው የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኘናቸው አቶ መታን አብዲራህማን፤ የዘንድሮው የምርጫ ሂደት እስካሁን የተቀላጠፈ እና ዘመናዊ አገልገሎት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በምርጫው እለት ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የመራጮች የምዝገባ ሂደት እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል።