ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም አስገብታለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኢ- ተገማችና ተለዋዋጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ብላ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቷን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።

በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ጦርነትና ዓለም አቀፍ ቀውስ የምርቶች ግዥና ዝውውር ላይ ችግር መፍጠሩ ይታወቃል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ የአፈር ማዳበሪያ ከሚጓጓዝባቸው መስመሮች መካከል የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ጦርነቱ በመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ፈተና መደቀኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ዓለም አቀፍ ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ማዳበሪያን በተመለከተ ቀደም ብሎ ዝግጅት በማድረግ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።


 

በዚህም ለዘንድሮ የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸምና በማጓጓዝ ወደ ህብረት ስራ ዩኒየኖችና አርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ የተሰራጨው የአፈር ማዳበሪያ 16 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል እንደነበር ገልጸው፤ ጅቡቲ የደረሰውን ጨምሮ ዘንድሮ 20 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ገብቷል ብለዋል።

የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥና የግብዓት አጠቃቀምን ለማሻሻል 30 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱን በመጥቀስ፤ ቀሪውን ለማሳካት ከወዳጅ ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብርና ስምምነት መፈጠሩን ገልጸዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ የግብርና ልማት ሰንሰለት ውስጥ ከምርት እስከ እሴት መጨመርና ገበያ ድረስ ያለውን ሂደት መቆጣጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የጀመረችው የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ግንባታ በተለዋዋጭና ኢ-ተገማች የዓለም ሁኔታ ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን በድል መወጣት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሮች በተፈጥሮ በሚዘጋጁ የኮምፖስት ማዳበሪያ ምርቶች ላይ በስፋት በመሰማራት ጫናውን መቀነስ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም