በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች ለምርታማነት እድገት እመርታዊ ለውጥ እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች ለምርታማነት እድገት እመርታዊ ለውጥ እያመጡ ነው
ባህርዳር፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቮች ለምርታማነት እድገት እመርታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የምርት እድገቱ በምግብ ራስን የመቻል ጥረትን ለማሳካት፣ ለኢንዱስትሪ ግብአትና የወጭ ንግድ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ፤ በክልሉ የግብርና ልማት እንቅስቃሴና ምርታማነትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በክልሉ የግብርና ልማት ከምርት ወቅቶች ባሻገር የበጋ መስኖ ልማትን በስፋት የመጠቀም፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የሌማት ትሩፋትና ሌሎችም ኢንሼቲቮች ለምርታማነት እድገት እመርታዊ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።
በግብርና ልማቱ በተለይም የኩታገጠምና የመካናይዜሽን እርሻ፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት መሟላት ለምርታማነቱ ማደግ ዋናውን ድርሻ መያዙን ጠቅሰዋል።
በ2012/2013 የመኸር ወቅት ቀደም ሲል በማካይ ይመረት ከነበረው 121 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል አሁን ላይ 188 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ መቻሉን ለአብነት ገልጸዋል።
በክልሉ የግብርና ልማትና ምርታማነት በአይነትም ይሁን በብዛት ከፍተኛ እድገት እየተመዘገበበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በክልሉ የመካናይዜሽን እርሻ እንዳልነበር አስታውሰው አሁን ላይ በድምሩ ከ2 ሺህ 888 በላይ ትራክተሮች፣ የሰብል ማጨጃና መውቂያ ኮምባይነሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አነስተኛ የሰብል መውቂያ፣ የሩዝና የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችን በመጠቀም በግብርና ልማትና ምርታማነት ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአማራ ክልል ከምርት ወቅቶች ባሻገር ማምረት የሚለው አስተሳሰብ ወደ ተግባር እየተቀየረ በመሆኑ፣ ግብርናው ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ንግድ ተኮር ግብርና እየተሸጋገረ ይገኛል።