ቀጥታ፡

ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ገለጹ። 

ምክር ቤቱ ግብርናውን የሚያዘምኑ ህጎችን በማውጣት ገንቢ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የዘንድሮ ሀገራዊ የበልግ እርሻ እና የመኸር የሰብል ልማት ማስጀመሪያ ንቅናቄ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ አስጀምረዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዲስ ኢኒሼቲቭ ነው።

ኢኒሼቲቩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው ብለዋል።  

ኢትዮጵያ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ልማት ሕልውናዋን እንድታረጋግጥ ታስቦ የተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የግብርናውን ሽግግር የሚያሳልጡ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰተጠው ስልጣን መሰረት ለግብርናው ሽግግር ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ በምክር ቤቱ አርሶ አደሩን የሚያበረታቱ፣ ግብርናውን የሚያዘምኑ ህጎች መፅደቃቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በአምራች አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች መካከል የፋይናንስ፣ የግብዓትና የዕውቀት ትብብር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የማያስችል የኮንትራት ፋርሚንግ/የእርሻ ውል/ አዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ መዋሉን አንስተዋል።

ከዚህም ባሻገር ምክር ቤቱ የአስፈፃሚ አካላትን በመቆጣጠርና በመከታተል እንዲሁም የተሰራውን በመገምገም ለዘርፉ እድገት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ጌቱ ገመቹ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠቱ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።

በኦሮሚያ ክልል ስንዴ አብቃይ ከሆኑ እንደ ባሌ ባሉት አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ስንዴ ለምቶባቸው በማያውቁ አካባቢዎች ጭምር ማልማት ተጀምሯል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ የሴፍትኔት መርሀ ግብር ተጠቃሚ የነበሩ አርሶ አደሮች ስንዴ በማልማት ትርፍ አምራች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በ2011/12 የምርት ዘመን ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አሁን ወደ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል ብለዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሲጀመር ከአርሶ አደሮች ባለፈ ምሁራን ጭምር ጥርጣሬ ነበራቸው ያሉት ቢሮ ሀላፊው፤ አርሶ አደሩ በዝናብ ላይ ከተንጠለጠለ ግብርና መውጣቱን ገልጸዋል።

የስንዴ መስኖ ልማት ውጤታማ በመሆኑ አርሶ አደሩ የመንግሥት መመሪያ ተቀብሎ በአግባቡ በመተግበሩ የመጣ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚታረስ መሬትና በምርታማነት ከመኸር ወቅት የተሻለ መሆኑንም አቶ ጌቱ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም