የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና የላሊጋ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና የላሊጋ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26/2018(ኢዜአ)፡- በስፔን ላሊጋ የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባርሴሎና ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ትኩረት ስቧል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ 70 ሺህ 692 ተመልካች በሚያስተናግደው ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ይካሄዳል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በሊጉ እስከ አሁን ካደረጋቸው 29 ጨዋታዎች በ17ቱ ድል ሲቀናው በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 49 ግቦችን ሲያስቆጥር 28 ጎሎችን አስተናግዷል። የማድሪዱ ክለብ በ57 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ባርሴሎና በበኩሉ 29 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ24ቱ አሸንፎ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዶ በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
78 ጎሎችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 28 ግቦች ተቆጥረውበታል። የካታላኑ ክለብ በ73 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የዛሬው ለ254ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ባደረጓቸው 253 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ባርሴሎና 116 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
አትሌቲኮ ማድሪድ 81 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 56 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በላሊጋው እስከ አሁን 178 ጊዜ ተገናኝተው ባርሴሎና 83 ጊዜ አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ 53 ጊዜ ሲያሸንፍ 42 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ማሸነፍ በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ባርሴሎና ድል ቀናው የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በተያያዘም በ69 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ ከሜዳው ውጪ ከሪያል ማዮርካ ጋር ከቀኑ 11 ሰዓት ከ15 ላይ ይጫወታል።
ዛሬ የሚደረጉ ጨዋታዎች በላሊጋው የዋንጫ ፉክክር ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።