ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደርጋሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከሲዳማ ቡና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ በዘጠኙ ተሸንፎ 11 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

15 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያሳርፍ 25 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ23 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና 24 ጨዋታዎችን አከናውኖ 12 ጊዜ ሲያሸንፍ በሶስቱ  ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 30 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ሲዳማ ቡና በ45 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው መቀሌ 70 እንደርታ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለምወጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኛል። 

ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ እና መሪነቱን ለማጠናከር ይጫወታል። 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ 24 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን ሲያሸንፍ በስምንቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

19 ግቦችን በ24ቱ ጨዋታዎች ላይ 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 18 ጎሎችን አስተናግዷል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ28 ነጥብ 14ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሊጉ ካከናወናቸው 23 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በተመሳሳይ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 23 ግቦችን ሲያገባ 24 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ቡናማዎቹ በ32 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ሁለቱም ቡድኖች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። 

ሀዲያ ሆሳዕና በ29 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሶስት ነጥብ ከዛሬው ጨዋታ ማግኘት ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ ያደርገዋል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ወላይታ ድቻ በ27 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ30 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በ24ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ድል ከቀናው ከወራጅ ቀጠና ይወጣል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም