ቀጥታ፡

ተጠባቂው የማንችስተር እና ሊቨርፑል የኤፍኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፡- በኤፍኤ ካፕ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 8 ሰዓት ከ45 ላይ ማንችስተር ሲቲ ከሊቨርፑል በኢትሃድ ስታዲየም ይጫወታሉ።

 

በጥሎ ማለፉ ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን፣ ሊቨርፑል ዎልቭስን ማሸነፋቸው ይታወቃል።

ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፕ ሲገናኙ የአሁኑ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ሊቨርፑል በአራቱ ድል ሲቀናው ማንችስተር ሲቲ ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1897 ሲሆን ሊቨርፑል 2 ለ 1 አሸንፏል።

በውድድሩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወቱት እ.አ.አ በ2022 በግማሽ ፍጻሜው ሲሆን ሊቨርፑል 3 ለ 2 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል። በፍጻሜው ቼልሲን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

ማንችስተር ሲቲ ለመጨረሻ ጊዜ ሊቨርፑልን በኤፍኤ ካፕ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2003 ሲሆን በሶስተኛው ዙር 1 ለ 0 አሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በውድድሩ ስኬታማ የሚባሉ ክለቦች ናቸው።

ማንችስተር ሲቲ ሰባት ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ፣ ሊቨርፑል ስምንት ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ፍልሚያ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል።

 

በሌላኛው መርሐ ግብር ሳውዝሃምፕተን ከአርሰናል ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሴንት ሜሪ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በጥሎ ማለፉ ሳውዝሃምፕተን ፉልሃምን፣ አርሰናል ማንስፊልድ ታውንን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብተዋል።

ሳውዝሃምፕተን አንድ ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል። አርሰናል ዋንጫውን 14 ጊዜ በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ክለብ ነው።

ባለሜዳው ሳውዝሃምፕተን በእንግሊዝ ሻምፒዮንሺፕ (ሁለተኛ ዲቪዚዮን) የሚገኝ ሲሆን አርሰናል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን እየመራ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በውድድሩ ባደረጓቸው 11 ጨዋታዎች አርሰናል ሰባቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ሳውዝሃምፕተን በሶስቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

 

ምሽት 1 ሰዓት ከ15 ላይ ቼልሲ ፖርትቫሌን በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ያስተናግዳል።

ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፕ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ቼልሲ የፕሪሚየር ሊግ፣ ፖርት ቫሌ የፉትቦል ሊግ ዋን (ሶስተኛ ዲቪዚዮን) ክለቦች ናቸው። 

የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን ስምንት ጊዜ አንስቷል። ፖርት ቫሌ በውድደሩ ትልቁ ውጤቱ ግማሽ ፍጻሜ ከመድረስ የዘለለ አይደለም።

154 ዓመታትን ያስቆጠረው ኤፍኤ ካፕ የዓለማችን አንጋፋ የእግር ኳስ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም