ቀጥታ፡

የጀጎል አለም አቀፍ ቅርስን የታደገው ሀገራዊ ለውጥ

የስልጣኔ መነሻ የጥበብ መፍለቂያ የሆነችው የምስራቋ ፈርጥ ሀረር የንግድ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ትስስር ማዕከል ሆና በትውልድ ቅብብሎሽ ከአንድ ሺህ አመታት በላይ የተሻገረች እድሜ ጠገብ ከተማ ነች።

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምስራቅ አፍሪካ የእስልምና ሀይማኖት ትምህርትና የንግድ ማዕከል የነበረችው ከተማዋ በርካታ ቋሚና ተንቀሳቃሽ እንዲሁም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቁሳዊና ሀይማኖታዊ ቅርሶችን የያዘች ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ነች። 

ከእነዚህ ቅርሶች መካከል ጥንታዊ የስነ-ህንፃ የጥበብ፣ የከተማ ፕላን፣ ባህላዊ የመሬት አጠቃቀም፤ አካባቢያዊ መስተጋብርና የስልጠኔ መገለጫ በሚል እኤአ በ2006 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ በአለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የጀጎል ቅርስ ይጠቀሳል፡፡


 

ቅርሱ ምንም እንኳን በኪነ ህንፃ ጥበብ በላቁ በአርቆ አሳቢ አባቶች እንዳይፈርስና ሚዛኑን ጠብቆ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ በተመረጠ ድንጋይ እና አፈር በልዩ ጥበብ የተገነባ ቢሆንም በጥበቃና እንክብካቤ ጉድለት ምክንያት ከግማሽ ምዕተ አመታት በላይ እድሜን ባስቆጠረው ቅርስ ላይ አደጋ ተጋርጦበት ቆይቷል።

በቅርሱ ውስጣዊ እና ውጫዊ ክፍሎች  የህገ-ወጥ ግንባታዎች መበራከትና በሌሎች ምክንያቶች በደረሰበት ጉዳት የጥንት ስልጣኔ ምልክት የሆነው አለም አቀፉ የጀጎል ቅርስ ከዩኔስኮ የአለም ቅርስነት እስከመሰረዝ የደረሰ አደጋ ተደቅኖበት ነበር።

ሆኖም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ እሳቤ፤ በተደመረ አቅምና በላቀ ቁርጠኝነት፤ ህዝብን በማሳተፍ ከመንግስት ምንም አይነት በጀት ሳይመደብለት ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ማልማት ተቻለ።

አሁን ላይ እነኛ በሸራና በጨርቅ በተሰሩ ህገወጥ ግንባታዎች ተወሮ የነበረው 3ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የጀጎል ግንብ ዙሪያ በአበቦችና ቅርሱን በሚያስውቡ ስራዎች ደምቀዋል።


 

በዚህም አባቶች ከዘመኑ ቀድመው ዛሬም ድረስ ግርምትን በሚያጭር ጥበብ አንፀው ያኖሩት ይህንን የሀገር ሀብት በመታደግ ትውልዱን ከታሪክ ተወቃሽነት ወደ ዳግም ታሪክ ሰሪነት እንዲሸጋገር ማድረግ ተችሏል።

ስራውም የትላንትን መሰረት ሳያናጋ፤ የቀድሞ አባቶችን ጥበብና ስልጣኔ ሳይጋፋና ሳይዘነጋ ጥንታዊውን ከዘመናዊ ጋር አዋህዶ ቅርስ መገኛ ለሆኑ ሌሎች አካባቢዎችም ተምሳሌት በሚሆን ደረጃ አስደናቂ ስራ ተከናወነ።

የአካባቢውን ሀብትና እውቀት በመጠቀም እውን የተደረገው ይህ ስራ በእያንዳንዱ የሀረሪ ጥንታዊ ቤቶች በሚገኙ የታሪክ አሻራዎችና የባህል መገለጫዎች እንዲደምቅም ሆኗል።

ይህ ትውልድ ተሻጋሪ ስራ ቅርሱን ከአደጋ ከመታደግ ባለፈ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከግለሰብ እስከ ማህበራትና የዳያስፖራ አባላት ድረስ ሁሉም በያገባኛል ስሜት አሻራውን ያኖረበት ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው።

ይህም በቅርሱ ላይ የእኔነት ስሜት እንዲጎለብት በማድረግ የእይታ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻለና ቀደም ሲል የነበሩ የግለኝነት አስተሳሰቦችን በመቅረፍ የወል እሳቤ እውን የሆነበት ፕሮጀክት ሆኖ ታይቷል።


 

ዛሬ ላይ እነኛ የቆሻሻ መጣያ የነበሩ እና በአካባቢው ለማለፍ ከባድ የነበሩ የጀጎል መንገዶች ፀድተው ውብ ሆነዋል። ይዘታቸውን ለቀው የነበሩ ቅርሶችም የአለም ቅርስነት ክብርና መስፈርትን በሚመጥን ደረጃ ታድሰዋል።

ዛሬ የጀጎል ነዋሪ እንደቀድሞ አካባቢውን ለቆ ለመሄድ ሳይሆን መኖርን የሚመርጥባት የወጣውም መመለስን የሚመኝባት ምቹ አካባቢ ሆናለች።

የመቻል ምልክት የትብብር ውጤትና የአብሮነት ጉልበት በተግባር የታየበት የጁገል መልሶ ልማት ጥንታውን መንደር ለነዋሪዎች ምቹ ለጎብኚዎች ተመራጭ የጉብኝት ስፍራ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

በለውጡ መንግስት በአዲስ መልክና ቀለም የተዋበው ጀጎል የሀረርን ቀደምት ስልጣኔ እየመሰከረ የሀገርንም ገፅታ እየገነባ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም