ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ቻይና በኢኮኖሚ ዘርፍ ፍሬያማ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘውንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ተመላከተ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር ዌይ ሁዋን ጋር በሁለትዮሽ እና የቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። 

አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የሁለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። 

በወንድማማችነት እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተው ይህ የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር በፈተና ወቅቶች ሳይበገር የዘለቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በቻይና እና በኢትዮጵያ መካከል በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በኢኮኖሚያዊ ትስስር ትልቅ ፍሬ ማፍራቱንም ተናግረዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ይህም በማኑፋክቸሪንግ፣ በመሰረተ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

ቻይና በፈታኝ ወቅቶች ጭምር ከኢትዮጵያ ጎን የምትቆም ቁርጠኛ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ለዚህም አድናቆታቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ቻይና ከአፍሪካ ጋር ላላት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቁልፍ ሚና መጫወቷን አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ለምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፏን እንድትሰጥ አፈ-ጉባኤው ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይና ብሔራዊ ሕዝባዊ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር ዌይ ሁዋን በበኩላቸው፤ የኢትዮ-ቻይና ጠንካራ ወዳጅነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ፣ አስተማማኝ እና ትልቅ የወደፊት ራዕይን የሰነቀ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸው ምርቶች ለንግድና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እጅጉን ጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ቻይና በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ እና በአዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር ኮሪደር ላይ የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። 

ከዚህ ባለፈም በሰው ኃይል ልማት እና በተለያዩ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመዋል። 

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጠንካራ እና ፍሬያማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሚና ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የጀመረችውን ጉዞ ቻይና እንደምትደግፍም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም