ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ቻይና የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ለመፈራረም ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሰረት የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ለመፈራረም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከቻይና የፋይናንስ ሚኒስትር ላን ፎአን ጋር በቤጂንግ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በዋናነት ትኩረት ያደረገው የኢትዮጵያን የዕዳ ክፍያ ሽግሽግ በማጠናቀቅ፣ ነባር ፕሮጀክቶችን በማፋጠን እና በአዳዲስ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ነው።

ሁለቱ ወገኖች በዕዳ ሽግሽግ ረገድ የኢትዮጵያን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር እና ለኢኮኖሚ እድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍን ተከትሎ የሁለትዮሽ ስምምነቱን ለመፈረም ያላቸውን ዝግጁነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና በመቀነስ ረገድ ትልቅ እመርታ እንደሆነ ተገልጿል።

ቀደም ብለው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እና የገንዘብ አጠቃቀሙ ቀልጣፋ እንዲሆን በውይይቱ ወቅት አጽንዖት ተሰጥቶታል።

የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተልና የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን በጋራ ለመፍታትም ተስማምተዋል።

በአዳዲስ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች ዙሪያ፣ በተለይም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ለመገንባት በሚቻልበት የገንዘብ ድጋፍ ላይ ፍሬያማ ምክክር ተደርጓል።

አውሮፕላን ማረፊያው በኢትዮጵያ፣ በቻይና እና በዓለም አቀፍ ገበያ መካከል ያለውን የንግድና የትራንስፖርት ትስስር እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሁለቱ አገራት ማዕከላዊ ባንኮች መካከል ስላለው ትብብርና ስለተደረሱ ስምምነቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በበኩላቸው የተደረሰው መግባባት ለሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይ የዕዳ ስምምነቱን ለመፈረምና የአውሮፕላን ማረፊያውን ፕሮጀክት ለማስጀመር በቴክኒክ ደረጃ በቅርበት ለመሥራት እንደተስማሙ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም