ቀጥታ፡

የለውጡ ትሩፋት - ግብርናን የሚያሻግረው ዕይታ

የለውጡ ትሩፋት - ግብርናን የሚያሻግረው ዕይታ

በአሸናፊ በድዬ 

በኢትዮጵያ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ልዩ ቀን ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል። ዕለቱ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበትና  ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ የተጀመረበት ነው። ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች መሠረታዊ ውጤቶችን እያስመዘገበችም ትገኛለች። በተለይ በሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም መሰረት ፈጣን፣ አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ለዚህም ነው ዕድገቱን ፈጣንና ተከታታይ ለማድረግ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተለይተው ወደ ሥራ የተገባው።    

እነዚህ ዘርፎች ኢኮኖሚው በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ እንዳይቀርና በማንኛውም ዓለም አቀፋዊ ጫና ውስጥ የማይናወጥ ጽኑ መሠረት እንዲኖረው ያደርጋል። በተለይም ግብርናው ለኢንዱስትሪው ግብዓት ሲያቀርብ፣ ቴክኖሎጂው ደግሞ የግብርናውን ምርታማነት ሲያሳልጥ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ደግሞ ለሌሎች ዘርፎች መስፋፋት ወሳኝ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ ሲያመነጭ የተቀናጀ የሰንሰለት አሰራር መዘርጋት ይችላል። በዚህ መሠረት፣ ከለወጡ ወዲህ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ገጽታ እየቀየሩ ያሉትን እነዚህን ዘርፎችና የታሪካዊ ቀኗን ትሩፋት በወፍ በረር እንመለከታለን።

1. ግብርና ፦ የስንዴ አብዮት

ግብርናው አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። ከለውጥ ማግስት በኋላ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ በዘርፉ ታሪክ ቀያሪ ስኬት እየተመዘገበ ይገኛል። የዚህ ስኬት ዋነኛ ማሳያ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈው የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት ነው።

    👉የቀድሞ ቅኝት፦ የዳራ እውነታዎችና የጥገኝነት ቀንበር

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ግብርና ገጽታ በእድገት ማነቆዎች የተጠፈረ ነበር። ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ አመቺ የአየር ንብረትና ብዙ የሰው ኃይል  እያላት ለዓመታዊ የፍጆታ ፍላጎቷ የሚሆን በቂ ስንዴ ማምረት አቅቷት ለዓመታት ቆይታለች። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚደርስ  የውጭ ምንዛሬ  ስንዴ በመግዛት  ከውጭ ለማስገባት ትገደድ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪኳ ነው። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያ የማምረት አቅም እያላት ለውጪ ምንዛሪ ወጪ  ዳርጓት ቆይቷል፤  በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚፈጠሩ የዋጋ መዋዠቆችና ጂኦ-ፖለቲካዊ ቀውሶች ተጋለጭነቷን አስፍቶት እንደነበር የሚታይ እውነት ነው።   

    👉የለውጡ ስትራቴጂና ቁርጠኝነት የስኬት ጅማሮ

    ይህ ቢያንስ በስንዴ ጥገኛ አድርጎን የቆየው ተግዳሮት ታሪክ በሚቀይር መልኩ አዲስ ምዕራፍ ያስከፈተው መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ነው።  በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነትና ያላሰለሰ ክትትል የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት የኢትዮጵያን ግብርና ከነበረበት ተግዳሮት አላቆ ዘመናዊና ውጤታማ ምዕራፍ ያሸጋገረው ጉዞ ጀምሯል። ለዚህ በአብነት የሚጠቀሰው  የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስትራቴጂ ነው።

  በ2011 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ የተጀመረው የመስኖ ስንዴ ልማት፣ ዘንድሮ አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል፡፡ የምርት መጠኑም ከ100 ሺህ ኩንታል ወደ 175 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ብሏል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት  በመኸር፣ በበልግና በመስኖ የሚለማው መሬት ስፋት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ካለው ጋር ሲነጻጸር እምርታዊ ለውጥ ማሳየቱን ማስተዋል ይቻላል። በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች ሆናለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ዓመት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢኮኖሚው ዘርፍ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን መግለጻቸውን ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የጀመረችው ስትራቴጂያዊ ንቅናቄ በሀገሪቷ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የምርት ዕድገት አስመዝግቧል። ይህም የዘርፉን ጉዞ ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ አላቆ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ እጥፍ እንዲልቅና ለሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነት ዋነኛ መሰረት እንዲሆን አስችሎታል።

    👉የምግብ ሉዓላዊነትና የሀገር ክብር

ዛሬ ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ስንዴ ለውጭ ገበያ መላክ የጀመረችበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ይህም የለወጡ ትሩፋት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን በማዳን፣ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያን ተደራዳሪነትና ክብር ከፍ አድርጓል። በተጨማሪም እንደ አረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋትና መሰል መርሃ-ግብሮች በዘርፉ እምርታዊ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።

2. ኢንዱስትሪ 

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይም አምራች ኢንዱስትሪው ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወዲህ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካትና ለውጭ ገበያ የሚሆን ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ላይ ያተኮረ ነው።

በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ አማካኝነት ከዚህ ቀደም ተዘግተው የነበሩ በርካታ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል። የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን (እንደ ሲሚንቶና ብረት) በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም በማደጉ የግንባታ ዘርፉን አነቃቅቷል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመነትን በመሳብ ለሺዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

3. ማዕድን 

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በሳይንሳዊ መንገድ በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን ለማሳደግ ከለውጡ ወዲህ ትልቅ ርብርብ እየተደረገ ነው።

የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰልና የሌሎች ማዕድናት ምርት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። በተለይ የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ቀንሷል።

በዘርፉ ሕገ-ወጥ ዝውውርን በመቆጣጠርና ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የመንግሥት ገቢ እንዲያድግ ተደርጓል።

4. ቱሪዝም 

ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመጪነትና ተግባራዊ ስራዎች ቱሪዝም በአዲስ መልክ የተወለደና ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ ሆኗል። ቀደም ሲል በታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ላይ ብቻ ተወስኖ የቆየው እንቅስቃሴ፣ አሁን ላይ ሰው ሰራሽ መስህቦችን በማካተት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን አረጋግጧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተገነቡት አንድነት፣ እንጦጦና ወዳጅነት ፓርኮች የአዲስ አበባን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ከመቀየራቸውም በላይ ለከተማ ቱሪዝም አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። 

በ"ገበታ ለሀገር" መርሃ-ግብር የተገነቡትና በቅርቡ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት እንደ ወንጪ (Eco-Tourism)፣ ጎርጎራ ያሉ መዳረሻዎች የሀገሪቷን የቱሪዝም ሀብት ወደ ክልሎች በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ስኬት አስመዝግበዋል።

በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የታላቁ ቤተ-መንግሥት የቱሪስት መዳረሻ እና በ"ገበታ ለትውልድ" ስር እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ዘርፉን ይበልጥ አጠናክረውታል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ፣ በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።  

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ያስታወቁት፤ አዲስ አበባን የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ በርካታ የልማት ሥራዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች ፍሬ ማፍራት በመጀመራቸው፣ በከተማዋ የሚካሄዱ ኩነቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 150 የሚሆኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኹነቶች በአዲስ አበባ የተካሄዱ ሲሆን፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን መግለጻቸው ይታወቃል።

ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የቱሪስት ፍሰት ጋር ተያይዞ ባለፉት ስድስት ወራት 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉን የገለጹ ሲሆን፤ መዲናዋን የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለኹነቶቹ መጨመር በተጨባጭ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በክልሎች ከተሞች እየተሰሩ ያሉት የኮሪደር ልማቶች ከተማዎቹን ልዩና ውብ ከማድረጋቸው ባሻገር ለቱሪስት መስህብ ሆነዋል።

5. ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ/ዲጂታል ኢኮኖሚ

ይህ ዘርፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያደርግ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለውጥ ወዲህ የደመቀ የለውጥ ሞተር ነው።

የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስኬቶች በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶች (ፓስፖርት፣ ንግድ ፈቃድና ታክስ ክፍያ) በበይነ-መረብ በመሆናቸው ሌብነትንና እንግልትን ይቀንሳሉ።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በ"ፋይዳ" መታወቂያ የታቀፉ ሲሆን፤ በ"ቴሌ ብር"ና መሰል አማራጮች የገንዘብ ዝውውር መዘመን ችሏል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ሥራ መግባት የአገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን ጨምሯል። 

የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይ የ2025 ስኬትን መሠረት በማድረግ አሁን ላይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) በስፋት የመጠቀም ግብ ወዳለው ቀጣይ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በ"ኢትዮ-ኮደሮች" መርሃ-ግብር አምስት ሚሊዮን ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት ለማሰልጠን እየተሠራ ያለው ሥራ ወጣቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እያደረገም ይገኛል።

እነዚህ አምስት ምሰሶዎች ተነጣጥለው የሚታዩ ሳይሆን አንዱ ሌላውን የሚደግፉ ናቸው። ይህ ታሪካዊ ለውጥ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ የሚያሸጋግር ስትራቴጂ ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ በራሷ የምትመገብና ለሌሎችም የምትተርፍ ጠንካራ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ታርካዊ ክንውን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም