ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም ለዲጂታልና ታዳሽ ሃይል ልማት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው

አዳማ ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎትን ከማስፋት ባሻገር ለዲጂታልና የታዳሽ ሃይል ልማት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ ቴሌኮም በአዳማ ከተማ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል በመገንባት በዛሬው እለት አገልግሎት አስጀምሯል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ በኢትዮጵያ የዲጂታልና የታዳሽ ሃይል ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ተገንብቶ በዛሬው እለት ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከልም የዚሁ ልማት ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዳማው ማእከል በአንድ ጊዜ 12 ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ የሚያደርግ አቅም እንዳለው ተናግረው በሌሎች አካባቢዎችም የማስፋት እቅድ መኖሩን ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከፈጣንና ዘመናዊ የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለዲጂታልና የታዳሽ ሃይል ልማት በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

በዚህም መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች  ቻርጀ ማድረጊያ ማዕከላትን በማስፋፋት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፤ የስማርት አዳማ ፕሮጀክት ተቀርፆ አሰራርና አገልግሎቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስደገፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት የኢትዮ ቴሌኮም አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው በከተማዋ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም