የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ሂደት ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የላቀ ድርሻ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ሂደት ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የላቀ ድርሻ አላቸው
ሆሳዕና ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ሂደት ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ተመለከተ።
"የሚዲያ ተቋማት ሚና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ በምርጫ ሂደት የሚዲያ ተቋማት ሚና እና ሃላፊነት እንዲሁም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በስፋት ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮሌጁ ዲን ታደለ አባተ፤ የሚዲያ ተቋማት ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በምርጫ ወቅት እና በድህረ ምርጫ ሂደት ግልጽና ፍትሃዊ መሆኑን የማሳየት ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ ፖሊሲና ፕሮግራም ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የጠራ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በምርጫ ሂደት ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ፣ የጥላቻ ንግግሮችንና የተሳሳቱ መረጃዎችን በማጋለጥ እውነታን በማረጋገጥ እንዲሁም እውነተኛና ሚዛናዊ የመረጃ ምንጭ በመሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናትና የጋዜጠኝነት መምህርና ተመራማሪ መልሰው ደጀኔ (ዶ/ር)፤ የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ሂደት ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የላቀ ድርሻ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ያሉትን ሂደቶች በተጨባጭ መረጃ በማስደገፍና እውነታዎችን በማረጋገጥ ተደራሽ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ በምርጫ ሂደት የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚዲያ ተቋማት እውነተኛና ሚዛናዊ የመረጃ ምንጭ በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ተመስገን ቶማስ (ዶ/ር)፤ የሚዲያ ተቋማት የሀሳብ ብዝሀነትን በማስተናገድ የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።
የጋራ ትርክትን በሚያጠናክሩና የሀገርን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያሳልጡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራት ይገባል ሲሉም አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብድልባር ኡስማን፤ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ለዘንድሮው የምርጫ ሂደት ስኬታማነት የላቀ ሚናቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ምሁራን ተሳትፈዋል።