ቀጥታ፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የጤና ሥርዓቱን የሚያዘምን አበረታች ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የጤና ሥርዓቱን የሚያዘምን አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለጹ።

በጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የጤና ኢኖቬሽን ማበልፀግያና በሀርቫርድ ጤና ስርዓት ኢኖቬሽን ሃካቶን ትብብር በአዲስ አበባ የተዘጋጀው የ2026 ዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።


 

ጉባዔው በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን "ሰው ሰራሽ አስተውሎት፤ ለላቀ የጤና ሥርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ከዛሬ መጋቢት 25 እስከ 26/2018 ዓ.ም ይቆያል።

በዚሁ ጊዜ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል ልማት የጤና ጥራትና ፍትሐዊ ተደራሽነትን በማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዲጂታል ዘርፍ የተወሰዱ የሕግና የአሰራር ማሻሻያዎችም የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት በማዘመን ተጨባጭ ውጤቶች ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።


 

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መነሻነትም ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎትን በማዳበር የጤና ተቋማትን የማዘመን ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የዲጂታል ፈጠራ አስቻይ ምኅዳርም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ መዋቅራዊ የአሰራር ለውጥ እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማነትን በማሳደግ ወሳኝ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዲጂታል ምኅዳሩን በማስፋት በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃብት የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጥቅም ላይ በማዋል የአገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ የሰውን ህይወት ለመታደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በዲጂታል ዘርፍ የተመዘገቡ አስደናቂ የዲጂታል ስኬቶችም ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታዘጋጅ ማስቻሉን አስረተድዋል።

በጉባኤው ላይ 60 ኢትዮጵያዊያን የጤና ሙያተኞች፣ የሶፍትዌር አልሚዎች፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች የጤና ሥርዓትን የሚያሻሽሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድድር እንደሚያቀርቡም አስታውቀዋል።

በቀጣይም የዲጂታል መሰረተ ልማትን በማስፋት የፈጠራና ክህሎት ዝንባሌ ያላቸው ዜጎችን የማብቃት ሥራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም