በክልሉ ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በመገንባት ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በመገንባት ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል
ደብረ ብርሃን ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በመገንባት ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት መደረጉን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የአስተዳደር ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ ምስረታን ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ አካሄዷል፡፡
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ባንችአምላክ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ ተቋምን በመገንባት ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተደርጓል።
በአሁኑ ወቅትም የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም በመዘርጋት ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የአስተዳደር ዳኝነት ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ማድረግና የአስተዳደር ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤን ማቋቋሙን አንስተዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ግንባታው አካታችነትን ያረጋገጠና የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የሰራተኞች የአስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች ውሳኔ የሚጸድቀው በሌላ አካል እንደነበር ጠቁመው በአዲሱ አሰራር ገለልተኛ የሆነ አግባብ ተቋቁሞ እንዲሰራ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ የሲቪል ሰርቪስ አሰራሩን በማዘመን ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአስተዳደር ፍርድ ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መመስረቱም በሰራተኞች የሚነሱ የመብትና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን ህግን መሰረት ባደረገ አግባብ ለመመለስ የሚረዳ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ተጠሪ ዳኛ አቶ ስለሺ አብርሃም እንዳሉት፤ በክልሉ የሲቪል ሰርቪስ የዳኝነት ስርዓትን ነፃ ገለልተኛና ተጠያቂ ማድረግ ጠንካራ ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት ይረዳል ብለዋል።
አሁን የተመሰረተው የዳኞች ጉባኤ በሰራተኞች የሚነሱ የጥቅማ ጥቅም፣ የመብትና ግዴታ ውል ጉዳዮችን ራሱን ችሎ በማከራከር ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
መድረኩ ዘጠኝ አባላት ያሉት የአስተዳደር ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ አባላትን በመምረጥ ተጠናቅቋል።