ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የከተማ ተራራ ላይ የብስክሌት ውድድርን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የከተማ ተራራ ላይ የብስክሌት ውድድር (City Mountain Bike Race) ሚያዚያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ  ይካሄዳል። 

"ሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ውድድር ዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (UCI) የውድድር መርሃ ግብር ውስጥ የተካተተና እውቅና ያለው ነው። 

ውድድሩ በአፍሪካ ሲካሄድ የኢትዮጵያው የመጀመሪያ መሆኑን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

ውድድሩ ሚያዝያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ዙሪያ ይካሄዳል።  

ውድድሩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ዋናው ውድድር መሆኑን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

በዓለም አቀፉ ውድድር ላይ ከ24 የአውሮፓ እና ከ10 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ60 እስከ 80 የሚደርሱ ምርጥ ብስክሌተኞች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያን የብስክሌት ስፖርተኞች በውድድሩ ተሳታፊ ናቸው። 

ይህም ኢትዮጵያን በዓመታዊው የዓለም አቀፍ የከተማ ማውንቴንባይክ ካሌንደር ውስጥ ከባርሴሎና በመቀጠል ሁለተኛዋ መዳረሻ ያደርጋታል።

የኤሊት ተወዳዳሪዎች (ወንድ እና ሴት) የጊዜ ሙከራ፣ የግማሽ ፍጻሜ እና የፍጻሜ ውድድሮች ይከናወናሉ። 

ውድድሩ በዓለም አቀፉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ሲሆን፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ይከታተሉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዋናው ውድድር አስቀድሞ ሚያዚያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁሉም ክፍት የሆነ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች የመሳተፍ እድል ያገኛሉ። 

በዕለቱ የአማተር ብስክሌተኞች፣ የልጆች እና የሰዓት ሙከራ ውድድሮች ይካሄዳሉ። 

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ባወጣው መረጃ  ዓለም አቀፍ ውድድሩን ለኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልጿል።

ውድድሩ ኢትዮጵያን ለዓለም ከማስተዋወቁ ባሻገር፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸውን ውድድሮች የማዘጋጀት አቅም እንዳላት በተግባር እንደሚያሳይ አመልክቷል። 

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በሀገራቸው ከዓለም ኮከቦች ጋር የመወዳደር እድል እንዲያገኙና ወደ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ እንዲሸጋገሩ ትልቅ ድልድይ እንደሚያገለግልም ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው። 

ለኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም