ቀጥታ፡

በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተናል- የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች 

ጋምቤላ ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ዘንድሮ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ  ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ሲወስዱ ያገኘናቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል፡፡ 

አስተያየታቸውን ከሰጡን የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ  ኮንግ ቾል  እንዳሉት ዘንድሮ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ በወቅቱ ወስደዋል፡፡ 


 

ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ መያዛቸው የምርጫው ጊዜ ሲደርስ የሚፈልጉትንና ለሀገር የሚበጀውን ሀሳብ የያዘውን ፓርቲንም ሆነ እጩ ለመምረጥ መብት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ 

የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በጥንቃቄ በመያዝ ለሀገር ይጠቅማል ብለው ለሚያምኑት እጩ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አኙት ኡቹዶ ናቸው፡፡ 


 

አቶ አብዱ አቡበክር በበኩላቸው፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ጊዜው ከማለፉ በፊት መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 


 

የመራጭነት ካርድ መውሰድ የዜግነት ሃላፊነትን ከመወጣት ባለፈ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አይነተኛ ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል፡፡

ዘንድሮ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ 

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ  እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም