ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እመርታዊ ውጤት አስገኝቷል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ ዜጎችን በሁለንተናዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ያደረገ እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራር አባላት ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንዴሞ እንደገለጹት መጋቢት 24/2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀ ታሪካዊ ዕለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዕለቱ ያስተላለፏቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትልም የመደመር እሳቤዎችም በለውጡ ዓመታት ወደተጨባጭ ውጤት መቀየራቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በፖለቲካ መስክ ዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት በዴሞክራሲና በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ የምክክር ምኅዳር በመፍጠር ወሳኝ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም ለብዝኅ የኢኮኖሚ ልማት ዕድል በመክፈት ጸጋዎችን ወደጥቅም በመለወጥ ዕድገትን እያፋጠነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የመደመር መንግሥት እሳቤ የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን አስቻይ ምኅዳር መፍጠሩንም አስረድተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና በጀት ክትትልና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ፤ ሀገራዊ ለውጡ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እመርታዊ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም በስደት የነበሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ሳይቀር ወደሀገራቸው ተመልሰው በፖለቲካው መስክ ንቁ ተወናይ የሚሆኑበትን ዕድል እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት የፖሊሲ አቅጣጫዎችም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ የሀገርን ዕድገት በጥራትና ፍጥነት መምራት የሚያስችል አቅም መገንባቱን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ለውጡ በተለያየ ምክንያት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በንግግር መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ ናቸው።

የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቁርሾዎችና አለመግባባቶችን በሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ መፍትሔ ለመስጠትም ወሳኝ መሰረት እየተጣለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን አንሰተዋል።

የምክር ቤት አባላቱ፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የምርታማነት አቅም በማስቀጠል ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን ያረጋገጠች ሀገር ለትውልድ ማሻገር የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም