የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተከናወኑ የምርምርና የቴክኖሎጂ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተከናወኑ የምርምርና የቴክኖሎጂ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተከናወኑ የምርምርና የቴክኖሎጂ ተግባራት በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ተጨባጭ ለውጥና የምርት ዕድገት እያስመዘገቡ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በዚህም በተተገበረው የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
ለግብርና ዘርፉ የተሰጠው ትኩረትና የተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ በምርምር ማዕከላት የሚገኙ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ወደ መሬት እንዲወርዱ እና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በለውጥ ጉዞ ውስጥ የግብርናው ዘርፍ በምርምርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መደረጉ ለአርሶና አርብቶ አደሩ የምርት ዕድገት መገኘት መሰረት ሆኗል።
ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ዓመታት ድርቅንና ተባይን መቋቋም የሚችሉ እንዲሁም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣት ለአምራቹ ማሰራጨቱን ገልጸዋል።
በዚህም አማካይ የሰብል ምርት ላይ አስገራሚ ለውጥ መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል በአማካይ 20 ኩንታል የነበረው የስንዴ ምርት ከ36 ኩንታል በላይ ማደጉን እንዲሁም በአማካይ 20 ኩንታል የነበረው የበቆሎ ምርት ወደ 45 ኩንታል ከፍ ማለቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ስኬት ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት ለረጅም ዓመታት በምርምር ማዕከላት ተወስነው የቆዩ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል፡፡
በተለይም በቆላማ አካባቢዎች በመስኖ የሚለሙ 10 አዳዲስ የስንዴ ዝርያዎች ስራ ላይ መዋላቸው ለምርታማነቱ መላቅ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
በእንስሳት ልማት በኩልም የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን ተደራሽ የማድረግና ላሞችን በማዳቀል የወተት ምርትን የማሳደግ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከምርት ዕድገቱ ጎን ለጎን የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው የአፈር አሲዳማነትንና ጨዋማነትን በመቀነስ ለምነትን የሚያስጠብቁ የተለያዩ የምርምር ስራዎች ተከናውነው ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡት የግብርና ምርምር ውጤቶችና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎች፣ የሀገሪቱን ግብርና ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር በኩል የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው ተመልክቷል።