ቀጥታ፡

በመጪው ሚያዚያ ወር በአብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ይኖራል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ በመጪው ሚያዚያ ወር በአብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመጠንና ሥርጭት የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዚያ 22/2018 ዓ.ም የበልግ ዝናብ በመጠንና ስርጭት ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድበት ወቅት መሆኑን ገልጿል።

በዚህም በመጪው ሚያዚያ ወር በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከቀደሙት ሁለት የበልግ ወራት በመጠንና ሥርጭት የተሻለ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር አስታውቋል።

ይህም የአየር ጠባይ ሁኔታ የበልግ አብቃይና ተጠቃሚ አካባቢዎች ለሚያከናውኑት የግብርና ሥራ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብሏል ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው።

በተለይም በተያዘው የመጋቢት ወር የሚስተዋለው ተከታታይ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ በቡቃያና በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች ምርታማነት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል።

በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የሚጠበቀው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለቦረና፣ ጉጂና መሰል ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ሰብል ልማት፣ ግጦሽ መሬትና የውሃ አቅርቦት ወሳኝ መሆኑንም አመላክቷል።

በዚህም የበልግ አብቃይ አካባቢ አርሶና አርብቶ አደሮች ማሳቸውን በማዘጋጀት የሚጠበቀውን አመቺ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለመጠቀም ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

በበልግ ዝናብ መዋዠቅ አዝማሚያ ምክንያት ዝናብ አጠር የሆኑ አካባቢዎች የሚያጋጥማቸውን ተከታታይ ደረቃማ ሁኔታ ለመቋቋም እርጥበትን በማሳ ማቆየት የሚያስችል ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ኢንስቲትዩቱ አስውገንዝቧል።

በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች በሚኖር ከባድ ዝናብ ሊፈጠር ከሚችል የመሬት መንሸራተት፣ የአፈር መሸርሸርና ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም