ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ሊቀ መንበርነትን ተረከበች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የእ.አ.አ አፕሪል 2026 የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት (AU PSC) ተዘዋዋሪ ሊቀመንበርነትን በይፋ መረከቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ሊቀ መንበርነቱን የተረከበችው ከኮትዲቯር ነው።

ኢትዮጵያ መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም  የምክር ቤቱን አጀንዳዎች በሊቀመንበርነት መምራት እንደምትጀምር ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ  እ.ኤ.አ. በ2025 በድጋሚ የምክር ቤቱ አባል ሆና ከተመረጠች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊቀ መንበር መሆን ችላለች።

በሊቀመንበርነት ቆይታዋ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በሚገኙ አገራዊ እና ወቅታዊ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን እንደምትመራ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያን ሊቀ መንበርነት በይፋ ለማብሰር እና አዲስ የተመረጡ የምክር ቤቱን አባላት ለመቀበል መጋቢት 29 ቀን  2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰብሳቢነት የሰንደቅ ዓላማ የማውለብለብ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2004 ምክር ቤቱ ከተመሰረተ ጀምሮ በአባልነት ስታገለግል የቆየች መሆኑን የጠቀሰው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ እ.አ.አ በ2025 በድጋሚ ለሦስት ዓመታት አባል ሆና መመረጧን አውስቷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ የምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣ በንቃት ስትሳተፍ መቆየቷ ተወስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም