ቀጥታ፡

በለውጡ መንግስት የተተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምርታማነትን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት አሳድጓል

ወልቂጤ ፤መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦በለውጡ መንግስት የተተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምርታማነትን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት ማሳደጉን የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ። 

ከለውጡ በፊት የግብርና ምርታማነት መጠነኛ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የግብርና አቅም ያልተለየበትና ተግባር ተኮር አልነበረም።

በዚህም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከዝናብ ጥገኝነት ትርጉም ባለው መልኩ ማውጣት አልተቻለም ነበር።

ሆኖም ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና አዳዲስ የእድገት ምንጮችን ለመክፈትና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማረም የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ውጤት አስመዝግባለች።

ይህንን በማስመልከት ኢዜአ ያናገራቸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በለውጡ መንግስት የተተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምርታማነትን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት አሳድጓል ብለዋል።

ምሁራኑ አክለውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቅ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከማላቅ ባለፈ የመደራደር አቅምን እንደጨመረም አመልክተዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ገብሩ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት የለውጡ መንግስት የተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምርትና ምርታማነትን በማጎልበት የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ናቸው፡፡

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ  ምርትና ምርታማነት በመጨመር ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ ወደ ውጭ  ጭምር በመላክ የዘርፉን ስኬት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በስኬት በማጠናቀቅ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው ጎልቶ እንዲወጣ በማስቻል የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ማሳደጉን ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በማጠናቀቅ፣ ቱሪዝም በማስፋፋት፣ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ታይቷል ያሉት ደግሞ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ያበኬር ናቸው። 


 

በገጠር የተተገበሩ ዘርፈ ብዙ  የልማት ተግባራት በርካቶችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገሩ እንደሚገኙም አንስተዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እየተተገበሩ ያሉት የገበታ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት በአካባቢ ጥበቃ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኮሪደር ልማት እና በስራ ዕድል ፈጠራ የተከናወኑ ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያሳደጉ መሆናቸውን ረዳት ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርቶች ላይ በማተኮር፣ ከውጭ ይገቡ የነበሩትን በራስ አቅም በመተካትና የውጭ ምንዛሪን ማዳን በለውጡ መንግስት እውን ሆነው ውጤት እየተመዘገበባቸው ካሉ ስኬቶች ተጠቃሽ መሆናችውም በምሁራኑ ተነስተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም