ሀገራዊ ለውጡ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በተደመረ አቅም ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ አስችሏል-የፀጥታና ደኅንነት ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በተደመረ አቅም ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ አስችሏል-የፀጥታና ደኅንነት ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተቋማት የተደረገው ሪፎርም ጠንካራ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በመፍጠር በተደመረ አቅም ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማስቻሉን የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ሀገራዊ፣ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፀጥታና ደኅንነት ምህዳሩን የገመገመው ብሔራዊ የደኅንነት ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ የተሳተፉ የፀጥታና ደኅንነት ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ማብራሪያ ተለዋዋጭ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ ሀገራዊ የፀጥታ ምህዳር መገንባቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት፥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ከተገበራቸው የሪፎርም አምዶች አንዱ ጠንካራና ገለልተኛ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት መገንባት ነው።
በሪፎርሙም ፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በሰው ኃይል፣በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በአደረጃጀት የላቁ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የለውጥ እርምጃዎች በሀገሪቱ ያለውን ፀጥታና ሰላም ለማፅናትና በቀጣይም ተልዕኮዎችን ለመሸከም የሚያስችል ተቋማዊ አቅም መፍጠር ያስቻሉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አለኝታ የሆኑ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት መገንባታቸውንም አብራርተዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው፥ ሀገራዊ የፀጥታ፣የመረጃና የደኅንነት ምህዳሩ በተቀናጀ አግባብ በስኬታማነት እየተመራ መሆኑን ተናግረዋል።
በሪፎርሙ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ከተከፋፈለ አስተሳሰብ ወጥተው በተደመረ አቅም ሀገራዊ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የላቀ ብቃት ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የዘርፉ ሪፎርም ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተካሄደ መሆኑንና በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የተለያዩ ፈተናዎችን በውጤታማነት በማለፍ እየተጠናከሩ መምጣታቸውንም ገልፀዋል።
ተቋማቱ ሀገራዊ፣ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተልዕኳቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ በመወጣት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የኦሮሚያ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፥ ሀገራዊ ለውጡ በፀጥታና ደኅንነት ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ያጠናከረ ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።
በክልል ደረጃም የነበሩ የፀጥታ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና የሕግ የበላይነት በማስፈን ረገድ ከፍተኛ አቅምና ውጤት ያመጣ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
ተቋማዊ ሪፎርሙ ሀገሪቱ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገጥማትን የፀጥታና ደኅንነት ጥቃት በብቃት ለመመከት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
የፀጥታና ደኅንነት ሪፎርሙ ተናባቢና ተደጋጋፊ ተቋማትን መፍጠር ያስቻለ መሆኑንም ነው የገለፁት።
የፀጥታና ደኅንነት አመራሮቹ አክለውም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የፀጥታና የደኅንነት ግብረ ኃይል እቅድ በማዘጋጀት እየሠሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችል አቅምና ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
ከስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሞክሮ በመነሳት፥ባለፉት ስምንት ወራት የፀጥታ መዋቅሩ የጋራ እቅድ አዘጋጅቶ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ምርጫውን በተሳካ መንገድ ለማካሄድ ምቹ የፀጥታና ደኅንነት ምኅዳር መፈጠሩን ተናግረዋል።
ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ምንም ዓይነት ስጋት እንዳይፈጠር ተቋማቱ ቅንጅታቸውን አጠናክረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።