የትግራይ ክልል የመጀመሪያ ዙር የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ስኬታማ ነው- ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል የመጀመሪያ ዙር የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ስኬታማ ነው- ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል የመጀመሪያው ዙር የባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ስኬታማ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የመጀመሪያ ዙር ከመጋቢት 23 ቀን 2018 ዓም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲያካሂድ ቆይቷል።
በመጀመሪያው ዙር የተሳተፉ የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት ያጠናቀሩትን አጀንዳ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት፥ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኩ በሁሉም አካባቢዎች በተደረጉ ስነ-ዘዴዎች መካሄዱን ገልጸዋል።
መድረኩ ስኬታማ መሆኑን ጠቁመው፤ ለመድረኩ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በመድረኩ ከ700 በላይ ተሳታፊዎች የታደሙ ሲሆን በርካታ ሀሳቦች መንሸራሸራቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፥ የትግራይ ክልል የባለድርሻ አካላት የመጀመሪያው ዙር የአጀንዳ ማሰባሰብ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰው፥ በቀጣይም የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እንደሚኖር ገልጸዋል።