ቀጥታ፡

በሀረሪ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ናቸው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦በሀረሪ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ገለጹ።

መጋቢት ወር የኢትዮጵያ የመለወጥ ፍላጎት እውን የሆነበትና የብልፅግና ጉዞ የተጀመረበት ወር ነው ብለዋል።

ለውጡን ተከትሎ የመደመር መንግስት ሀገር መምራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ፣በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መስኮች እመርታዎች ተመዝግቧል ብለዋል።

በፖለቲካ ረገድ ከለውጡ በኃላ በክልሉ ከሴራ ፖለቲካ ወደ መርህ ፖለቲካ፣ ከመገፋፋትና ከጥላቻ ወደ ሰላምና አብሮነት እንድንሸጋገር አድርጎናል ብለዋል።

በኢኮኖሚ ረገድም በግብርና እና በቱሪዝም ልማት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም የትምህርት ጥራት ከማጎልበትና የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ከማረጋገጥ አንጻር የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ሃላፊው ገልጸዋል።

አደጋ ተጋርጦበት የነበረው አለም አቀፉ የጀጎል ቅርስ ከአደጋ መታደግ የተቻለው በእነዚህ የለውጥ ዓመታት ነው ብለዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የክልሉን ህዝብ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

በከተማው እና በጀጎል መልሶ ማልማት የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ከማሳደግ ባለፈ ለነዋሪዎች የተመቸች እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ለቀጣዩ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም