ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በሁሉም መስክ ልቆ መገኘትና ትብብርን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያንና የቀጣናውን ደኅንነትና ጥቅም ለማስከበር በሁሉም መስክ ልቆ መገኘትና ትብብርን ማጠናከር ወቅታዊና አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን ይህን ያሉት ትናንት በተካሄደው ሁለተኛው የብሔራዊ ደኅንነት ኮንፈረንስ ላይ ነው።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ባለፉት ዓመታት የፀጥታ ሁኔታው ተለዋዋጭ፣ኢ-ተገማችና ውስብስብ ክስተቶችን ማስተናገዱን አስታውሰዋል።

በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎችና አሸባሪ ቡድኖች የተለያዩ ችግሮች ሲፈጥሩ መቆየታቸውንም ነው ያነሱት።

የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን የማያባራ አዙሪት ውስጥ ለማስገባት ሙከራዎች ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።

የፀጥታና ደህንነት የተቋማት ስጋቶችን ለመከላከል፣ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማስቻል፣ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር፣ውጤታማ ስምሪትና የሕግ ማስከበር እርምጃ በመውሰድ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ተልዕኳቸውን በስኬት በመወጣት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ መሆኑን በመጥቀስ፤ በጎረቤት ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት መባባሱን፣በሶማሊያ እንደ አልሸባብና አይ ኤስ ያሉ አሸባሪዎች ማንሰራራታቸውንና የጥቃት ስልታቸውም እየተለዋወጠ መምጣቱን አንስተዋል።

በሌሎችም የክፍለ አህጉሩ ሀገራት የተለያዩ የፀጥታ ስጋቶችና ሁከቶች መጨመራቸውን ነው ያመለከቱት።

በዚህ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነው ዓለም አቀፍ ምህዳር ውስጥ የሀገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ለማረጋገጥ ልቆ መገኘት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

የውስጥ አቅምን በትብብርና በቅንጅት በማሳደግ ለሀገራዊ ተልዕኮ የሚሰማራ ኃይልን ማብዛትና ማጠናከር ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ለቀጣናው አዲስ ስጋት ፈጥሯል ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፥በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የባህር በር በሌላቸው ሀገራት ሁኔታውን ውስብስብ አድርጎታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር መዳረሻ ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ወቅታዊ የጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፎች በፍጥነት ከመቀያየራቸው ባሻገር ቀጣናው በቀይ ባሕር ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በሚፈልጉ ኃይሎች የፉክክር መናኸሪያ እየሆነ መምጣቱ ተጨማሪ ስጋት ደቅኗል ነው ያሉት።

ሁኔታው የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከወደብ በላይ በቀጣናው አስተማማኝ የፀጥታና ደህንነትን የሚያረጋገጥ አንድምታ እንዳለው አመላካች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቀይ ባሕር ተደራሽነት ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን ሁሉም የቀጣናው ሀገራት በትብብር መስራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ለማረጋገጥ በዲፕሎማሲው መስክ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል የግድ ሆኗል ነው ያሉት።

ይህ ቁልፍ ብሔራዊ የደኅንነት አጀንዳ እውን እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት የትኩረት መስካቸውን ከወቅታዊና ዘላቂ ፍላጎቶች አኳያ በመቃኘት የበኩላቸውን ሚና የመወጣት ወሳኝ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን፣ብሔራዊ ጥቅሞቿ እውን እንዲሆኑ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተደማጭነቷ እንዲያድግ እየሠራ ነው ብለዋል።

በሰው ኃይል፣በአሠራር፣ በአደረጃጀትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተቋማዊ ቁመናውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት አጀንዳዎችን ለማሳካት ከሁሉም የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ቅንጅታዊ አሠራር የጋራ ስምሪትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።

ተመሳሳይ ጥቅምና የጋራ ዓላማ ካላቸው የሌሎች ሀገራት አጋር አካላት ጋር ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም እንዲሁ።

ቀጣናው ባለብዙ ፍላጎቶች ያሉበት ስትራቴጂክ ስምሪት የሚካሄድበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የፈጠሩትን አጋጣሚ ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል እየሞከሩ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያንም ለማዳከም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረው መቀጠላቸውን መገንዘብ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እጅ ለእጅ ተያይዞ ለመሻገር በሲቪል፣ በፀጥታና በዜጎች መካከል ትብብርን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም