መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የሴፍቲኔት ተረጂ የነበሩ አርሶ አደሮች በስንዴ ልማት ትርፍ አምራች ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የሴፍቲኔት ተረጂ የነበሩ አርሶ አደሮች በስንዴ ልማት ትርፍ አምራች ሆነዋል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የሴፍቲኔት ተረጂ የነበሩ አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና በሌሎችም ምርቶች ትርፍ አምራች መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ገለጹ።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ፣በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳአ ወረዳ በበጋ መስኖ የለማ የስንዴ ማሳን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።
ቀደም ሲል እንደ ባሌ ባሉ ስንዴ አብቃይ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ስንዴ ተመርቶ በማያውቅባቸው አካባቢዎችም ጭምር በስፋት ማልማት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህ ስር ነቀል ለውጥ በክልሉ የሴፍቲኔት መርሃ-ግብር ተጠቃሚ የነበሩ አርሶ አደሮች ከራሳቸው ፍጆታ ባሻገር ወደ ትርፍ አምራችነት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በ2011/12 የምርት ዘመን በሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ተጀምሮ የነበረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አሁን ላይ ወደ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ማደጉን ገልጸዋል፡፡
ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ ታላቅ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የመንግሥትን መመሪያ ተቀብሎ በአግባቡ በመተግበሩ ውጤታማ መሆን መቻሉንና ይህም የኢትዮጵያ የሰብል ልማት ዘርፍ የት መድረስ እንደሚችል ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ እየተከናወነ ያለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሚታረስ መሬት ስፋትም ሆነ በምርታማነት ረገድ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡