የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ የነዋሪዎችና የጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ የነዋሪዎችና የጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ተጨባጭ ውጤት እየስገኘ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ የነዋሪዎችና የጸጥታ መዋቅር ቅንጅት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።
"ሕብረ-ብሔራዊነታችን ለአብሮነታችንና ለሰላማችን" በሚል መሪ ሐሳብ የአዲስ አበባና የሸገር ከተማ ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫና የልምድ ልውውጥ መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሄዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎን ጨምሮ የሁለቱ ከተሞች ከፍተኛ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ነዋሪዎችና የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት በመንቀሳቀሳቸው ለሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡
በተለይም ወሰን ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ረገድ የተከናወኑ ውጤታማ የቅንጅት ተግባራት ለተመዘገበው ስኬት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች መካከል ያለው የጸጥታ መዋቅርና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን ጠቁመው በቀጣይም ይበልጥ ስኬታማ ለመሆን ይህ አንድነትና ሕብረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው የተመዘገቡ ስኬቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለሰላም ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጉዮ ገልገሎ በበኩላቸው፤ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው፤ ሰርቶ መለወጥ ነግዶ ማትረፍ ወልዶ ማሳደግ የሚቻለው ሰላምን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ሲቻል ነው ብለዋል።
ለዚህም የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በጋራ በመስራታቸው ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ውጤታማ ስራ መሥራታቸውን ጠቅሰው በቀጣም ይበልጥ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ የመረጃ ምንጭ በመሆን ከጸጥታ አካላት እና ሰላም ሰራዊት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ሀጂ ሸምሱ አባስ በሰጡት አስተያየት መንግሥት በሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲጠናከር ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ፓስተር ጠና በየነ በበኩላቸው፤ የኃይማኖት አባቶች ስለ ሰላም የመስበክ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና በሸገር ከተማ አስተዳደር በጋራ በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ የሰላም ሠራዊት አባላት፣ ጋቸና ሲርና ፣ ሚሊሻዎችና ከሁለቱም ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።